የጅማ ዴዶ - መጠንሶ ጭዳ መንገድ በመበላሸቱ እየተጉላሉ መሆናቸውን መንገደኞች ተናገሩ

77
ጅማ፣ የካቲት 3/2012 (ኢዜአ) ከጅማ ዴዶ - መጠንሶ ጭዳ ያለው መንገድ በመበላሸቱ በትራንስፖርት እጥረት እየተጉላሉ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ መንገደኞች ተናገሩ። ከመንገደኞች መካከል አቶ ከድር ሁሴን እንደገለጹት መንገዱ በመበላሸቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት በዴዶ መናኸሪያ ውስጥ ለሰዓታት መጠበቅ የተለመደ ችግር ሆኗል፡፡ "ከመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳም ባለንበረቶች አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት በማጣታቸው እጥረቱን አባብሶታል"ብለዋል። ሌላው መንገደኛ ወይዘሮ ቡልቱ አወል በበኩላቸው የመንገድ ደህንነት ችግር በከፋ ሁኔታ የሚታየው ከጅማ ዴዶ ድረስ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ "በተለይም እናቶች፣ አዛውንቶችና ህመምተኞች ተጋፍተው መሳፈር የማይችሉ በመሆኑ የበለጠ ተጎጂዎች ሆነዋል" ብለዋል፡፡ የዴዶ ወረዳ መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ ተማም የመንገዱን ደህንነት የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጠን መሆንን ገልጸዋል፡፡ መንገዱ በ2010 ዓ.ም ጥገና የተደረገለት ቢሆንም ጥራት የሌለው በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ማገልገል እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡ የመንገዱ ባህሪ በየስድስት ወሩ ጥገና የሚፈልግ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጅማ መንገድ አውታር ደህንነት ዳይሬክተር አቶ መሰረት ደጀኔ በኩላቸው  82 ኪሎ ሜትር ሽፋን ያለው መንገዱ በግብዓት እጥረት ምክንያት የጥገና ስራውን በወቅቱ ለመጀመር አለመቻሉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ለጥገናው 18 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ጥገናው መጀመሩን አመልክተው "እስከ መጪው ግንቦት ተጠናቆ ችግሩ ይፈታል " ብለዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም