ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና በአዲስ አበባ አዲስ ኢምባሲ ልትገነባ ነው

165
አዲስ አበባ የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ እና የጋና አቻቸው ናና አኩፎ ለጋና ኤምባሲ ግንባታ የመሰረት ደንጋይ አስቀምጠዋል። ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና ጋና በፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ ታሪካዊና ፖለቲካዊ አበርክቶት በሁለትዮሽ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር መድገም እንዳላባቸው ተናግረዋል። በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ የሚገኙት የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ፤ ከኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሣህለወርቅ ዘውዴ ጋር ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ለሚገነባው አዲስ የአገሪቱ ኤምባሲ ማምሻውን መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል። ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴና ፕሬዝዳንት ኩዋሚ ንኩርማ ለፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄና ለአፍሪካዊያን ተቋማት ግንባታ እውን መሆን የመሪነት ሚና እንደነበራቸው በሁነቱ ላይ ተወስቷል። ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው ታሪካዊና ፖቲካዊ የኢትዮ-ጋና ግንኙነት በጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ጉዳዮች ድል ያስመዘገቡና ለሌሎች ተምሳሌት የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ተናግረዋል። ሁለቱ አገራት ያላቸውን ታሪካዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት በምጣኔ ሃብታዊ መስክ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከጋና ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ኤምባሲው በአጭር ጊዜ እንዲገነባ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ። ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጋና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጊዜ ጀምሮ በእምነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት መስርተው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል። ኤምባሲው በተለይም ከአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት አቅራቢያ መሆኑ እንዳስደሰታቸውም ገልጸው፤ የሁለትዮሽና በአፍሪካ አህጉራዊ ጉዳዮች በቅርበት ለመምከርም የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያና የጋና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ እና በቀድሞው የጋና ፕሬዝዳንት ኩዋሚ ኑኩርማ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም