አፍሪካ ኢኮኖሚዋን በማዘመን ሙስናና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል ትችላለች

67

አዲስ አበባ የካቲት  2/2012  (ኢዜአ) አፍሪካ ኢኮኖሚዋን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመደገፍ ሙስናና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል እንደምትችል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

የመንግስታቱ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት አፍሪካ በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ምክንያት በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ኢኮኖሚን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ዲጂታላይዝ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

አፍሪካም ከዘመኑ ጋር ለመራመድና ኢኮኖሚዋንና ማህበራዊ ልማቷን ለማፋጠን ወደ ዲጂታላይዜሽን አሰራር መግባት አለባት ነው ያሉት።

"በቀደሙት ዘመናት በአህጉሪቷ ግልጽነት የጎደለው አሰራር በመኖሩ የገንዘብ ብክነት፣ ሙስናና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲበራከት አድርጓል" ሲሉም አመልክተዋል።

"ይህ ሁኔታ ሊገታ የሚችለው ኢኮኖሚውን ዲጂታላይዝ በማድርግ ነው" ያሉት አቶ ኃይለማርያም ይህ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፍናል ይላሉ።

ከምንም በላይ ይህ መንገድ የአህጉሪቷ ወጣቶች በዘርፉ ያላቸውን እውቀት ጥቅም ላይ እንዲያውሉና እነሱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን አፍሪካ ወጣቶቿ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ እሴት የሚጨምር ነገር እንዴት መስራት እንዳለባቸው ማሳወቅም ይጠበቅበታል ብለዋል።

"ወጣቶች ይህን ከተገነዘቡ ደግሞ በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው ሃብት ያፈራሉ እንጂ በአቋራጭ መክበሪያ መንገዶችን አያስቡም" ሲሉ አስረድተዋል።

በአፍሪካ አገራት ቢዝነስ መጀመርና መስራት ከባድ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኃይለማሪያም "ዲጂታላይዜሽን የገንዝብ ዝውውርን ያፋጥናል፣ የቢዝነስ ሥራን ቀላል ያደርገዋል" ብለዋል።

ይህን ታሳቢ በማድረግ የአፍሪካ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ከሚጠበቀው 33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ዲጂታላይዝ በሚሆንባቸው መንገዶች ላይ ውይይቶች ተካሂደዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም