ኢትዮጵያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የነፃ ቨዛ ስምምነት ተፈራረሙ

398

አዲስ አበባ የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ኢኳቶሪያል ጊኒ የዲፕሎማቲክና የአገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ዜጎች ቪዛ እንዳይጠየቁ ተስማሙ።

ኢትዮጵያና ኢኳቶሪያል ጊኒ የዲፕሎማቲክና የአገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ዜጎች ቪዛ እንዳይጠየቁ ተስማሙ።

ከአፍሪካ ህብረት 33ኛው መደበኛ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው የኢትዮጵያና የኢኳቶሪያል ጊኒ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የጊኒው ፕሬዚዳንት ቲኦዶር ኦቢያንግ ንጉኤማ ምባሶጎ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ መሰረት ባደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያና ኢኳቶሪያል ጊኒ የዲፕሎማቲክ የአገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ዜጎቻቸው ቪዛ እንዳይጠየቁ የአገሮቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፊርማቸው አረጋግጠዋል።

በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢኳቶሪያል ጊኒ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝቱ የሁለቱ አገሮች መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ከስምምነቱ ውስጥ የዲፕሎማቲክና የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ የሁለቱ አገሮች ዜጎች ቪዛ ማስቀረት አንዱ ነው።

ከውይይታቸው በኋላ የኢኳቶሪያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሞን ኦያኖ አንጌ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የቪዛ ነጻ ስምምነቱን ፈርመዋል።

ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል በተለያዩ ጉዳዮች ለይ በጋራ ለመስራት በፊርማቸው ቢያረጋግጡም ከአየርና ተያያዠ ጉዳዮች በቀር ሌሎችን ወደ ተግባር አልተቀየሩም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ በረራ አለው።

የዛሬው ስምምነት በተለይ የዴፕሎማቲክና የአገልግሎት ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ አገሮች ዜጎች ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላቸዋል ተብሏል።

ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የፈረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመለወጥ ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰሜን፣ ምዕራብ የማዕከላዊ የደቡባዊ አፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ አክሊሉ ከበደ ለኢዜአ ገልጸዋል።