” ብክለትም ብክነትም "

100
ገብረሀይወት ካህሳይ ኢዜአ በምሽት ጭፈራ ቤቶች ፣ በእምነት ተቋማት ፣ በምርትና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ፣ በእርዳታ ጥሪዎች……… የሚለቀቁ ከልክ ያለፉ ድምፆች ሰላም የሚነሱ ፣ ጤናን የሚያውኩና የተኛ የሚቀሰቅሱ ናቸው ። በተለይ በአገራችን ትላልቅ ከተሞች ልኬቱ የማይታወቅ ድምፅ ስለሚለቀቅ ቅሬታ የሚያሰሙ ነዋሪዎች በርካታ ቢሆኑም ሰሚ ሲያገኙ አልታየም ። ሰሚ ያጡትንም ቢሆኑ ችግሩን ከመልመድ የዘለለ አማራጭ የላቸውም ። ከላይ የተጠቀሱት ከመጠን ያለፉ ድምፆች የድምፅ ብክለት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ያልተፈለገ ድምፅ በጉዞ ፣ በእንቅልፍ ፣ በስራና በትምህርት ፣በንግግርና መሰል የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅእኖ ያሳድራሉ ። ጤናማ ከባቢን በመበከል በስነ ልቦናዊና አካላዊ ጤንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጭምር ነው - የድምፅ ብክለት ። ሆኖም ግን የድምፅ መጠን እንደ ሰሚው ዕድሜ ፣ እንደ ግለሰቦች የጤና ሁኔታ ፣ እንደ ድምፁ ቆይታና ድግግሞሽ የሚለያይ ነው ። ለአንዱ መደበኛ ድምፅ ለሌላው የሚረብሽ ፤ለአንዱ የሚረብሽ ድምፅ ለሌላው ሙዚቃ ሊሆን ይችላል ። ኢትዮጵያ የድምፅ መጠን ለመወሰን የሚያስችላት መመሪያ አውጥታለች ። የብክለት አዋጅም አላት ። በድምፅ ብክለት ዙርያ ያለውን ችግር ለመፍታትም ደንብ ተዘጋጅቷል ። በደንቡ ላይ በሚያወጡት የድምፅ መጠን መሰረት የመኖሪያ ፣ የንግድ ፣የኢንዱሰትሪና ቅይጥ በሚል ተከፋፍለዋል ። በህጉ መሰረት በመኖሪያ ቤት የሚለቀቀው ድምፅ በቀን 55 በሌሊት ደግሞ 45 ዲሲ ቢል መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል ። ዲሲ ቢል የድምፅ መለኪያ መሳሪያ ነው ።በንግድ አካባቢዎች በቀን 65 ሌሊት 57 በኢንዱስትሪ አካባቢ ደግሞ በቀን 75 ሌሊት ከ70 ዲሲ ቢል መብለጥ እንደሌለበት ተቀምጧል ። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቤተሰብ ጤና ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር የሺመቤት ዓሊ እንደሚሉት ከሆነ ከ20 እስከ 80 ዲሲ ቢል የሚደርስ የድምፅ መጠን ጤናማ ነው ። ከዚያ በላይ ከሆነ ግን የጆሮ ታንቡርን በመብሳት የመደንቆር ጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል ። ከመጠን ያለፈ ድምፅ በአእምሮና በጆሮ ነርቭ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ። ድምፁ ድንገተኛ ከሆነ ደግሞ ራስህን በማሳት ጭምር ለጤና ችግር ያጋልጣል ይላሉ ።በተለይ ተደጋጋሚ ኃይለኛ ድምፅ ለዘላቂ የጤና ችግር መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ ። ነገር ግን አሁን የሚለቀቀውን ድምፅ ጎጂ መሆኑን ለማወቅ ዲሲ ቢል በሚባለው የድምፅ መለኪያ መጠኑ መታወቅ አለበት ባይ ናቸው ። ካልሆነ ግን ሁሉንም የድምፅ ዓይነቶች ጎጂዎች ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም ይላሉ ። የድምፅ ብክለቱ ሲያሳስበን ኧረ ብክነትም ጭምር ነው የሚሉን ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው ። በከተማው የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ጋሻው አህመድ እንደሚሉት ለሰርግ ስነስርዓት ማድመቂያ ተብሎ የሚተኮሱ ሮኬቶችና ርችቶች የከተማውን ሰላም ክፍኛ እያወኩት ይገኛሉ። የከባድ መሳሪያ ያክል የሚፈነዱ አውቶማቲክ ሮኬቶች የፀጥታ ችግር ቢከሰት እንኳን ለመስማማትና ለመረዳዳት በሚያዳግት መልኩ ከልክ ያለፈ ድምፅ ያስተጋባሉ ። ድምፁ ሰላማችንና ጤንነታችን ጭምር እየተፈታተነ በመሆኑ መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ነው ይላሉ ። ደስታን በልኩና ሰውን በማይረብሽ መልኩ መግለፅ እየተቻለ በየጊዜው የሚያጋጥመው ከፍተኛ የድምፅ ብክለት የሚከላከል አካል መጥፋቱ አግባብነት እንደሌለው አቶ ጋሻው በአፅንኦት ይገልፃሉ ። የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሃያት መሃመድ ደግሞ አስተያየት የሚሰጡት ከራሳቸው ገጠመኝ በመነሳት ነው ። ባለፈው ወር በአንድ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ድንገት በተተኮሰ ሮኬት በድንጋጤ ራሳቸውን ስተው በመውደቅ ለጤና ችግር ተጋልጠው እንደነበር ያስታውሳሉ ። ”የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል " ይባል የለ ? በየቦታው በሚተኮሱ ርችቶች ሽፋን ጥይት የሚተኩሱና ሆነ ብለው ግርግር በመፍጠር ለዝርፊያ የሚወጡ ቀማኞች መኖራቸውንም ወይዘሮዋ ትዕዝብታቸውን አጋርተውናል ። መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል መፍትሔ እንዲፈልግለትም በድምፁ ሁካታ የተረበሹት የደሴ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል ። የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መመሪያ ኃላፊ ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው ሙህዬ እንደሚሉት ደግሞ የሰርግ ስነ ስርዓትን ለማድመቅ ሲባል በተደጋጋሚ የሚተኮሱ ርችቶችና ሮኬቶች በመደበኛ የፀጥታ ስራ ሳይቀር ጫና እየፈጠሩ ነው ። በተለይ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከጥይት በላይ ድምፅ የሚያወጡ ሮኬቶች መኖራቸው የጸጥታ ስጋት የሚፈጥርበት አጋጣሚ መኖሩን ያስረዳሉ ። የፀጥታ ችግር ቢፈጠር እንኳን ህብረተሰቡ ሮኬት ነው በሚል ወጥቶ እንዳይተባበር በማድረግ ለጥፋት ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ። ችግሩ ከመሰረቱ መፈታት ስለሚገባው በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቡን በማሳተፍ እልባት እንዲያገኝ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ከዋና ኢንስፔክተሩ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ። የደሴ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበራ አሉላ በጉዳዩ ዙርያ በሰጡት አስተያየት ከድምፅ ብክለት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ብክነት እያስከተለ ነው ። ህብረተሰቡ አላስፈላጊ ፍክክር ውስጥ ገብቶ እስከ 7 ሺህ ብር ድረስ የሚሸጡ ሮኬቶችን በመግዛት ይጠቀማል ። ይህ ደግሞ ተገቢ ያልሆ ወጪ ነው ብለው ያምናሉ ። በእለት ከእለት የፀጥታ ስራው ላይም ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ የሚቆምበትን መንገድ በጥናት በመለየት በቅርብ ቀን እንዲፈታ ይደረጋል ። በአንድ በኩል ብክለት በሌላ በኩል ደግሞ ብክነት ማስከተሉ ሳያንስ የፀጥታ ችግር ሆኖ ብቅ ማለቱ ደግሞ አሳሳቢነቱ እንዲጎላ አድርጎታል ። በሰው ልጅ የህይወት ዘመን ውሱን አጋጣሚዎች ብቻ የሚፈጥሩት የሰርግ ስነስርዓት ደምቆ እንዲያልፍለት የማይፈልግ ሰው የለም ። ነገር ግን በልኩና ኢትዮጵያዊ ባህላችን በተከተለ አግባብ ቢፈፀም ደግሞ የበለጠ ያደርገዋል ። በሌላ መልኩ ደግሞ ስለአንተ ደስታና ዝና ስትጨነቅ የህብረተሰቡን ሰላምና ጤና ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ። በጋብቻህ እለት የሚመርቅህ እንጂ የሚረግምህ ህዝብ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ። በደስታ ስካር በሚፈጠር ስህተት የህግ ተጠያቂነትም ሊያስከትል ይችላልና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም ። በተደጋጋሚ ጊዜ በሚለቀቀው ከልክ ያለፈ የድምፅ መጠን በሌላ ሰው ጤንነት ላይ ጉዳት መድረሱ ከተረጋገጠ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ህጋችንም ያስጠይቃል ። ጉዳት አድራሹ ለተጎጂው ወገን ተገቢውን ካሳ መክፈል እንዳለበት ተደንግጓል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም