አፍሪካ የንግድ ስርዓቷን በቴክኖሎጂ ማገዝ ግድ ነው

49
አዲስ አበባ ኢዜአ የካቲት  2/2012   አፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴዋ በአህጉሪቷም ይሁን ከተቀረው ዓለም ጋር የተሳለጠ እንዲሆን የኤሌክትሮኒክ ግብይትን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባት ተጠቆመ። ከ33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን "አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባት የዲጂታል ሽግግሩን አስቻይ ማድረግ" በሚል ሃሳብ ውይይት ተካሂዷል። ትኩረቱን ኤሌክትሮኒክ ግብይት ላይ ባደረገው የውይይት መድረክ የሕብረቱ የንግድ ጉዳይ ኃላፊዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአባል አገራቱ ተወካዮች ተሳትፈዋል። የአፍሪካ ኢ-ንግድ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉዓለም ስዩም እንደሚሉት የወቅቱ የንግድ እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ መታገዝ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ አህጉሪቷ እስካሁን ወደኋላ የቀረች መሆኑን ጠቅሰው የኤሌክትሮኒክ ንግድ ቡድኑም ይህንኑ ለማሳለጥ እየሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የአህጉሪቷ ፖሊሲ አውጪዎች ለዲጂታል ኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታዎችን ለማዘጋጀት አተኩረው መስራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት። የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሕብረቱ በጋራ ሊተገብረው ያቀደውን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናም ውጤታም እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት። አቶ ሙሉዓለም እንዳሉት ነጻ የንግድ ቀጣናው ወደ ሥራ የገባው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ገበያተኞችን በማገናኘት ያገበያያል በሚል ግምት ነበር። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሁሴን ሀሳን እንዳሉት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2016 አፍሪካዊያን እርስበርስ የፈጸሙት የፍጆታ እቃ ግብይት መጠን ከ12 ነጥብ 9 ወደ 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። "አህጉሪቷ ለምግብ ፍጆታ ብቻ ከ2012 እስከ 2017 በየዓመቱ 49 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋ ከሌሎች ክፍለ ዓለማት አስገብታች" ሲሉም አብራርተዋል። የኤሌክትሮኒክ ግብይቱ የተጠናከረ ቢሆን አህጉሪቷ ለዚህ ሁሉ ብክነት እንደማትዳረግ ያመለከቱት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ "ንግድን ማዘመኑ የተሻለ መፍትሄ ነው" ብለዋል። "የንግዱን ዘርፍ ማዘመኑ መካከለኛና ጥቃቅን ሥራ ፈጣሪዎችም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የጎላ ሚና ይጫወታል" ብለዋል። ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊ አገራትና የግሉ ዘርፍ ተወካዮችም ንግድን በቴክኖሎጂ ማገዙ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም