የጾታ እኩልነትን ሳናረጋግጥ የምንፈልጋትን አፍሪካ መፍጠር አንችልም – የቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት

982

የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የጾታ እኩልነትን ሳናረጋግጥ የምንፈልጋትን አፍሪካ መፍጠር አንችልም ሲል የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ ከ33ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን 24ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።

የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሊቀመንበርን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኒጀር ቀዳማዊ እመቤት አይሳታ ኢሱፉ ማሃመዱ የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 እቅዱና በሌሎች ስትራቴጂዎቹ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‘’ነገር ግን አሁንም በአፍሪካ ሴቶች ከወንዶች እኩል በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች መስኮች ያላቸው ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጪነት ዝቅተኛ ነው’’ ብለዋል።

‘’ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ሴት አመራሮች በተቋማት ውስጥ የውሳኔ ሰጪነትን እንዳያገኙ የሚደረግ ጫናና መገለል እንዲሁም ጥራት ያለው የጤናና የትምህርት አገልግሎት አለማግኘት የአፍሪካ ሴቶችን እየገጠሟቸው ያሉ ዋነኛ ፈተናዎች ናቸው’’ ብለዋል።

‘’የሴቶች እኩል ተጠቃሚነትና የጾታ እኩልነት ሳናረጋግጥ የምንፈልጋትን አፍሪካ መፍጠር አንችልም’’ ሲሉ ነው ቀዳማዊ እመቤቷ የገለጹት።

በዚህም ረገድ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን በማሳደግ ሴቶችን ማብቃትና የጾታ እኩልነትን ማረጋጋጥ ላይ በትብብርና በቅንጅት መስራት ያስፈልገዋል።

የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2023 ተግባራዊ ስትራቴጂ ቀርጾ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቀረት፣ ጾታዊ ጥቃት የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች እንዲሻሻሉ ማድረግና ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቀር ማድረግ ላይ በተሰሩ ስራዎች ለውጥ መታየቱን አውስተዋል።

የአመለካከትና የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የፋይናንስ ተደራሽነት በስራዎች ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውንና በቀጣይ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግና ተሰሚነታቸው እንዲጨመር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚስ አሚራ ኤልፋዲል የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት ሴቶችን ለማብቃትና ጾታዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ ለሚሰሩ ስራዎች ተቋማዊ አቅምና ምቹ መድረክ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

‘’የጦር መሳሪያን ድምጽ ማጥፋት በሚለው የ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እሳቤ ውስጥ በአፍሪካ በሚከሰቱ ግጭቶች አብዛኛው የጉዳት ሰለባ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት ናቸው’’ ብለዋል።

ሴቶች በግጭቶች ተጎጂ እንዳይሆኑ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግጭቶችን መንስኤ በመለየት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጾታዊ እኩልነት አለመረጋገጥ፣ ማህበራዊ ፍትህ ማጣት፣ ዝቅትኛ የልማት ተደራሽነት፣ የስራ አጥነትና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች የግጭቶች መነሻ መንስኤ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የችግሩን መንስኤ ከምንጩ ለማድረቅ ሴቶች በተቋማት ቁልፍ የውሳኔ ሰጪ ቦታዎችን እንዲያገኙ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነታቸው እንዲያድግና የጾታ እኩልነት እንዲረጋገጥ በህብረቱ ፖለሲዎችና ህጎች እንዲሻሻሉ ለማድረግ ከአባል አገሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

‘’የምንፈልጋትን አፍሪካን ለመፍጠር ግጭቶችን ማስቆም፣ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል፣ እኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባናል’’ ያሉት ሚስ አሚራ ኤልፋዲ፤ ከዚህ አንጻር ያሉ ክፍተቶች እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ወክለው የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ‘’ኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ የተለያዩ አበረታች ስራዎችን እያከናወነች ነው’’ ብለዋል።

ሴት ፕሬዚዳንት በመምረጥ፣ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በመሾምና በካቢኔ ውስጥ ያላቸውን ውክልና በማሳደግና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ ማስገባቷን ጠቅሰዋል።

አጀንዳ 2063 ውጤታማ እንዲሆን የአፍሪካ ሴቶች ማብቃት ወሳኝ እንደሆነና ለዚህም ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት እንዲያድግ እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አክለዋል።