በአፍሪካ የህክምና ኤጀንሲ እንዲቋቋም የሚያስችለውን ሥምምነት የፈረሙ አገራት 14 ደረሱ

77
አዲስ አበባ የካቲት 1/2012 (ኢዜአ)  በአፍሪካ የህክምና ኤጀንሲ እንዲቋቋም የሚያስችለውን ሥምምነት የፈረሙ አገራት 14 ማድረሳቸውን በአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኢልፋዲል ገለጹ። የአፍሪካ ኅብረት የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ እንዳይገባ ከቻይና መንግሥትና ከኅብረቱ አባል አገራት ጋር በመሆን የመከላከል ሥራ ላይ ርብርብ እይተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። የአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኢልፋዲል ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ የህክምና ኤጀንሲ እንዲቋቋም ባለፈው ዓመት ሥምምነት ላይ ተደርሷል። ኤጀንሲው በአፍሪካ መድሃኒት ለማምረት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀትና የአባል አገራት የዘርፉ ተቋማትና ባለሙያዎች አቅምን ለማዳበር ያስችላል ብለዋል። በየአገራቱ የሚወጡትን የፋርማሲ ዘርፍ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለማጣጣምና ተመጋጋቢ ለማድረግም የኤጀንሲው አስፈላጊነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የጠቆሙት። በአገሪቱ ከደረጃ በታች የሆኑ መድሃኒቶች እንዳይመረቱና ገበያ ላይ እንዳይወጡም ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ በምትኩ ጥራት ያለው መድሃኒቶችን በብዛት ለማምረት ያስችላል ነው ያሉት። በተለይም በአፍሪካ የመድሃኒት ምርትን በማስፋት የኢንዱስትሪውን ልማት ለማቀላጠፍ እንደሚያስችል ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የኤጀንሲውን አስፈላጊነት በማመን እስካሁን 14 አገራት መፈረማቸውን ገልጸው ፈራሚዎቹ 15 ሲደርሱ ኤጀንሲው በአህጉር ደረጃ እንደሚቋቋም ነው የገለጹት። የኮሮና ቫይረስን በመተለከተ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑና ወደ ቻይና ቀጥታ በረራ ያላቸው 15 አገራት ተለይተው ከአገራቱ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ቫይረሱን ለመቋቋም በተደረገ ጥረት በአሁኑ ወቅት ከቤልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የአምስት ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸው ገንዘቡን ለአቅም ግንባታ ይውላል ብለዋል። የቻይና መንግሥትም በዚህ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የኮሮና ቫይረስ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የቤተ-ሙከራ ምርመራ የሚደረገው በደቡብ አፍሪካ መሆኑን አስታውቀው ይህንን የህክምና አገልግሎት ለማስፋት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የህጻናት የጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል የሚያስችል የ10 ዓመታት ስትራቴጂ መቀየሱን ገልጸው ይህም ኮሚሽኑ ከደረሰበት ትልቅ ስኬት አንዱ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ኅብረቱ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በሊቢያ በስደት ላይ የነበሩ ከ48 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል። ሌሎች አምስት ሺህ ስደተኞች ደግሞ ከሩዋንዳ መንግስት ጋር ስምምነት ተደርጎ በአገሪቱ ተጠልለው እንደሚገኙና ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በአፍሪካ ህገ-ወጥ ስደትንና የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችሉ በአህጉሪቱ ሶስት የጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲከፈቱ ውሳኔ መተለላለፉንም ነው የገለጹት። በዚህም መሰረት በሞሮኮ፣ ማሊና ሱዳን ማዕከሎቹ እንደሚከፈቱ ጠቁመው ከአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በኋላ ማዕከሎቹ የሚቋቋሙበት ህገ-ደንብ እንደሚጸድቅ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም