የአፍሪካ ሴቶች በሰላምና ደህንነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና የሚሰጥ መጽሐፍ ተመረቀ

1098

አዲስ አበባ፣ የካቲት 01/2012 ( ኢዜአ ) የአፍሪካ ሴቶች በሰላምና ደህንነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና መስጠቱን ዓላማ ያደረገ የመጀመሪያው መጽሐፍ ተመረቀ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ኳርቴይ ቶማስ ክዌሲ ትናንት ምሽት መጽሐፉን በይፋ መርቀውታል።

“ሴቷ ለሰላም ተነስታለች ፣ 20 ዓመታት 20 ጉዞዎች” የሚል ርዕስ አለው መጽሐፉ። መጽሐፉን የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋራ አሳትመውታል።

ሁለቱ ተቋማት መጽሐፉን ያሳተሙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2000 ያፀደቀውን የውሳኔ ሀሳብ 20ኛ ዓመት ለማስታወስ ነው።

የውሳኔ ሀሳቡ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላምና ደህንነት ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና የሰጠና አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሕግ ማዕቀፍ ያስቀመጠ ነው።

የተጻፉት ታሪኮች ሠላም ማስከበርና ግንባታ ላይ እየሰሩ ላሉ አፍሪካዊያን ሴቶች ተነሳሽነት ለመፍጠርና ጠንክረው እንዲሰሩ ለማበረታታት የሚያግዙ እንደሆኑ ተገልጿል።

መጽሐፉ በተመረቀበት ወቅት የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

መጽሐፉ የተመረቀው ከ33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በተዘጋጀ መድረክ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረት በሥራና ደህንነት ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከርና ማሻሻል ላይ ዓላማ ያደረገ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2017 መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።