የፌዴራልና የክልል መንግስታት ግንኙነትን የሚመራ ግልጽ ፖሊሲ አለመኖሩ ለህግ የበላይነት አለመከበር በር ከፍቷል

69
አዲስ አበባ፣ የካቲት 01/2012  ( ኢዜአ ) በፌዴራልና ክልል መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት የሚመራበት ግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖሩ ለህግ የበላይነት አለመከበር በር ከፍቷል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝምና የህግ ምሁራን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አካሄዷን ለውጣለች። በርካታ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው ፣ በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ፣ በመንግስት እጅ የነበሩ ግዙፍ ኩባንያዎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት መሆናቸው ከተለወጡ ሂደቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን በዚህ የለውጥ ሂደት "የህግ የበላይነት ይከበር" የሚለው ሃሳብ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እስከ ህዝብ ድረስ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ሆኗል። የሚመለከታቸው አካላት "መንግስት በሆደ-ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው" በማለት  ለጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡም ይደመጣል። ኢዜአ ከዚህ አንጻር "የህግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ዋነኛው እንቅፋት ምንድን ነው" ሲል የፌዴራሊዝም ምሁር የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ኃይለኢየሱስ ታዬን እና የህግ ባለሙያ አቶ አሮን ደጎልን አነጋግሯል። ባለሙያዎቹ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በህግ አለመመራቱ ችግሩን እንዳባባሰው ነው የሚያብራሩት። ረዳት ፕሮፌሰር ኃይለኢየሱስ እንደሚሉት፤ ፌዴራሊዝም የጋራና የግል ጉዳይ ያላቸውን ህዝቦች አስተሳስሮ ለማኖር ተመራጭ አስተዳደር ነው። በመሆኑም ስርዓቱን የሚተገብሩ አገሮች በሚያዋቅሯቸው አስተዳደሮች መካከል ያለውን የግልና የጋራ ኃላፊነት በህገ-መንግስታቸው እንደሚያስቀምጡ ተናግረዋል። በህገ-መንግስቱ ያልተካተቱ ቀሪ ስልጣኖችን ማን ይውሰደው የሚለው በህገ-መንግስት እንደሚወሰን ገልጸው፤ ፊዴራሊዝምን የሚከተሉ በርካታ አገራት ይህን ስልጣን ለፌዴራል መንግስት ይሰጣሉ ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ይህ ስልጣን ለክልሎች መሰጠቱን አብራርተዋል። ከዚህ የተነሳም ክልሎች ፈርጣማ ጉልበት አዳብረዋል ይላሉ። በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት የፌዴራልና ክልል መንግስታት የፓርቲ መስመርን በመጠቀም ጉዳዮቻቸውን ሲያስፈጽሙ እንደነበርም አውስተዋል። በአሁኑ ወቅት ይህ የፓርቲ መስመር ግንኙነት መፍረሱን ጠቁመው፤ ግንኙነቱን የሚተካ የተደራጀ መንግስታዊ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ አለመሆኑ ደግሞ ሁሉም እንደፈለገ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት። የህግ ባለሙያው አቶ አሮን ደጎል በበኩላቸው ባለፉት ስርዓቶች ህግን ሽፋን በማድረግ የዜጎችን መብት መጣስ የተለመደ አካሄድ እንደነበር ተናግረዋል።አክለውም ለውጡን ተከትሎ አፋኝ ህጎችንና ተቋማትን በማሻሻል ረገድ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸውን ትእዛዞች ተከታትሎ በማስፈጸም ረገድ አሁንም ክፍተት መኖሩን አውስተዋል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በፌዴራልና ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያስቀምጥ ግልጽ የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው። የህግ የበላይነት ጉዳይ በአፋጣኝ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም