ማቀዝቀዥ የተገጠመላቸው አራት ዘመናዊ የዓሳ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ለአገልግሎት ተዘጋጁ

ኢዜአ ጥር 30/2012   በአማራ ክልል በዓሳ ማስገር ለተሰማሩ ማህበራት የዓሳ ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚያጓጉዙባቸው አራት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ለአገልገሎት ተዘጋጁ። የክልሉ እንስሳት ሃብት ኤጀንሲ ለኢዜአ እንደገለጸው  ዘመናዊ ፍሪጅ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎቹ ከ15 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጭ  ተገዝተው የቀረቡ ናቸው። ዓሳ ለማዕከላዊ ገበያ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ  ይውላሉ። ከተሽከርካሪዎቹ መካከል ሦስቱ  በዋግህምኸራ ብሄረሰብ አስተዳደር  ሳህላ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች  ለአስጋሪዎች ማህበራት የሚተላለፉ ቀሪው ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ዓሳ አጥማጅ ማህበር የሚሰጥ ናቸው። እያንዳንዱ ተሽከርካሪም  60 ኩንታል የዓሣ ምርት ማጓጓዝ  እንደሚችሉ በኤጀንሲው የዓሳ ሃብት ልማት ባለሙያ አቶ አራጋው አምባው አስረደተዋል። ማህበራቱ በአካባቢያቸው ካለው ሰው ሰራሽ ግድብ በርካታ መጠን ያለው ዓሣ እያመረቱ ቢሆንም በቀላሉ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው ለኪሳራ ሲዳረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል። በዚህም  ከእያንዳንዱ ወረዳ በቀን እስከ አስር ኩንታል ዓሳ ለብልሽት ይዳረግ እንደነበረም ባለሙያው ጠቅሰዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት  የክልሉ መንግስት  ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው ፤ ከክልሉ  ዘላቂ ልማት ግብ ፕሮጀክት በተገኘ የበጀት ድጋፍ ተሽከርካሪዎቹ መገዛታቸውን ገልፀዋል። በተገባደደው ሳምንት ውስጥ ባህርዳር የገቡት ተሽከርካሪዎቹ በቅርብ ቀን ለዓሳ አስጋሪ ማህበራቱ ተላልፈው  ለአገልግሎት እንደሚበቁ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ለዓሣ አስጋሪ ማህበራቱም ከዚህ በፊት ወደ ሰው ሰራሽ ግድቡ የሚያደርስ መንገድ መሰረት ልማትና የዓሣ ምርት ማጠራቀሚያ ሸዶች መሰራቱንም ባለሙያው  አስታውሰዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም