የሴቶችና ሀፃናት የስነ ልቦና ህክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

78
መቀሌ ኢዜአ ጥር 30/2012፡- በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት የስነ ልቦና የህክምና ማዕከል ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ። ማዕከሉን ያቋቋሙት የትግራይ ክልል ሴቶች ጉዳይ እና ጤና ጥበቃ ቢሮዎች ከባለድርሻ አካላት ጋ በመተባበር ነው። የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል በምርቃቱ ስነ ስርዓት ወቅት እንደገለጹት የማዕከሉ አገልግሎት መጀመር በአስገድዶ መደፈር ሳቢያ በሴቶችና ህጸናት ላይ የሚደርሰባቸውን ጉዳት ለማከም ያግዛል። ማዕከሉ በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚደርሰው ግርዛት ፤ያለ ዕድሜ ጋብቻና የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ለማስቀረትም ይረዳል ብለዋል። በተለይም ከአሁን ቀደም  በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞ በቂ ማስረጃና መረጃ አልቀረበበትም እየተባለ የሚዘጉ መዝገቦች በማስቀረት ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶክተር የትምወርቅ ገልጸዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት በቀላሉ ወደ ማዕከሉ መጥተው የህክምና ምርመራና የስነልቦና ምክር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ተወካይ ወይዘሮ ቤተልሄም ከበደ ድርጅታቸው ለማዕከሉ ማቋቋሚያ 600 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ገነት ኪዳነ በበኩላቸው የማዕከሉ አገልግሎት መጀመር በሴቶችና ህጻናት ጉዳት ደርሶ ሲደበቅ የነበረውን አጋልጦ  በህግ እንዲታይ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። የማዕከሉ መቋቋም ከአቃቤ ህግና ሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ያግዘናል  ያሉት ደግሞ የህጻናትና ሴቶች ጥቃት መርማሪ ኢንስፔክተር ሳምራዊት ሚሊዮን ናቸው። የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ዶክተር ሓጎስ ጎድፋይ "እንዲህ ዓይነት ማዕከል ሲቋቋም በክልሉ  ለመጀመሪያ ጊዜ ነው" ብለዋል። በማዕከሉ የሚሰሩ የህክምናና የስነ ልቦና ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ መመደባቸውንም ጠቁመዋል። በቀጣይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች  ተመሳሳይ  አገልግሎት የሚሰጡ  ስድስት ማዕከላት ይሰራሉ ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም