መቋጫው የተቃረበው የህዳሴ ግድብ ድርድር

130
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከተበሰረበት አንስቶ  ግብፅ ለህልውናዋ እጅግ አደገኛ  እንደሆነ መወትወቷን ቀጥላለች።

በተቃራኒው  ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ መጠቀም ሉዓላዊ መብቷ መሆኑን እና የተፋሰሱ አገራትንም የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ ማድረጓን  ታስረዳለች፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለተፈረሙ የቅኝ ግዛት እና ድህረ ቅኝ ግዛት ኢፍትሐዊ ውሎች እውቅና እንድትሰጥ ሲደረጉ የነበሩ ሙከራዎችንም እንደማትቀበል  በማስረገጥ።

አሁን  የግድቡ ግንባታ ከ70 በመቶ በላይ መጠናቀቁ  “ኢትዮጵያውያን የህዳሴውን ግድብ በራሳቸው አቅም ገንብተው ማጠናቀቅ አይችሉም” የሚለው የግብጽ የተዛባና የተሳሳተ ግምት ተቀይሮ የድርድር አጀንዳው በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ ላይ ያተኮረ ሆኗል።

በመሆኑም ሶስቱ አገራት ከበርካታ ዙር ውይይቶችና ድርድሮች በኋላ በአሁኑ ወቅት ወደ መቋጫ የቀረቡ ይመስላል።

በያዝነው ዓመት በጉዳዩ ዙሪያ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ የውይይትና የድርድር መድረኮች በሶስቱ አገራት መካከል የተካሄዱ ቢሆንም በዋናነት በአሜሪካና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች በተገኙበት የተካሄዱት ሶስት ተከታታይ መድረኮች ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ ደረጃ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት የተፈጠረባቸው መሆኑን የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች የሰጡት መግለጫ ያስረዳል።

ይህም ሆኖ በየመድረኮቹ በተለይ በግብጽ በኩል በሚመጡ አዳዲስ ሃሳቦች ምክንያት ስምምነቱን መቋጨት እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ በኩል የህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ከ4-7 አመታት ውስጥ ግድቡን ለመሙላት ሃሳብ ሲቀርብ ግብጽ በበኩሏ ከ12-21 አመታት ውስጥ ግድቡን እንድትሞላ ሀሳብ በማቅረቧ እንዲሁም በውሃ አለቃቅና በድርቅ ወቅት ስለሚኖረው ሁኔታ ድርድሩ ቀጥሏል ።

እነዚህን ልዩነቶች በማጥበብ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ በአሜሪካና በዓለም ባንክ አደራዳሪነት አራተኛ ስብሰባቸውን ከጃንዋሪ 28-29 በዋሽንግተን ዲሲ ለማካሄድ ተገደዋል።

በዚሁ መድረክ የሶስቱ ሀገራት የውጭ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የመጨረሻ የተባለውን ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ቢጠበቅም ወደ መግባባት መቃረባቸውን እንጂ ስምምነት አለመፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ፍራንስ 24 የተሰኘው ሚዲያ ግብፅ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከ10 አመት በላይ እንዲራዘም እና እንዲዘገይ እንዲሁም አስዋን ግድብ ላይ ለሚኖረው ተጽእኖ ዋስትና እንዲሰጣት ያቀረበችው ጥያቄ ኢትዮጵያን ማስቆጣቱና ተቀባይነት አለማግኘቱ ስምምነቱ ከበድ እንዲል እንዳደረገው በዘገባው አመልክቷል።

አያይዞም ግብጽ የአባይን ውሃ የብሄራዊ ደህንነቷ ዋነኛ ማጠንጠኛ አድርጋ መውስዷ ድርድሩን አስቸጋሪ ስለማድረጉም በዋሽንግተን የታህሪር የመካከለኛው ምስራቅ ፖሊሲ ተቋም ተመራማሪ ቲሞቲ ካልዳስን በዋቢነት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ሶስቱ ሃገራት አካታች ያሉትን እና በአሜሪካና በአለም ባንክ አደራዳሪነት የሚከናወነው የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ስምምነት ከመካሄዱ አስቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ግብጽ ለአሁኑና ለመጭው ትውልድ ውሃን የመጠቀም መብቶች አስጠብቃ እንደምትሄድ መግለጻቸው ድርድሩ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳሳደረም ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡

 በሌላ በኩል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ም/ቤት አባል የሆኑት አምባሳደር አሚን ሻላቢ አሽራቅ አል አውሳት ለተባለው ጋዜጣ እንደገለጹት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት መሞከራቸው ጥሩ የሚባል ቢሆንም የግብጽን ፍላጎት ግን ሙሉ በሙሉ ግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአፍሪካ ኒውስ ድረ-ገጽ አስተያየታቸውን የሰጡት የሱዳኑ የመስኖ እና የውሃ ሃብቶች ሚኒስትር ያሲር አባስ እንዳሉት በግድቡ የውሃ አሞላል እንዲሁም የድርቅ ወቅት ለሚለው  ሃረግ ስለሚሰጠው ትርጉም ሶስቱም ሃገራት የተራራቀ ሃሳብ ማቅረባቸው ድርድሩን ባለመስማማት እንዲያሳድሩት ስለማድረጉ አንስተው ውሃውን ለጋራና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማዋል በሚለው ጽንሰሃሳብ ተደራዳሪዎቹ መግባባት ላይ ስለመድረሳቸው ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ ሶስቱ ሃገራት ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ከስምምነት ላይ መድረስ ከቻሉ በዓለም ላይ ከሚታዩ ውዝግቦች መካከል አንዱና ዋነኛው ለሆነው ችግር መፍትሄ ስለመገኘቱ ማሳያ ይሆናል ሲሉ ዘግበዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያና የግብጽ አቋም እጅግ የተራራቀ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ የሚሉም አልጠፉም።

የአፍሪካን በአፍሪካ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደቡብ አፍሪካን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ በዚህ ወር ቀጣዩ የ2020 የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በመሆናቸው ደቡብ አፍሪካ አደራዳሪ ሆና በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንድትገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አገራቸው ስምምነት ሊደረስባቸው የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ረገድ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ስለመሆንዋ ገልጸው ነበር። “የአባይ ወንዝ ለሶስቱ ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ እናም ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል የተራራቁ ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀራርቡበት መንገድ መኖር አለበት” ሲሉም አክለዋል።

በእርግጥ ካይሮ አፍሪካን በሚመለከት በቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ላይ መቆሟ ሁለት ወሳኝ ፈታኝ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ እንዳስገደዳት አመላካች ነገሮች መኖራቸውን ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የመጀመሪያው ግብፅ የምታራምደው አቋም ከሰሃራ በታች ካሉ የላይኛው የናይል ተፋሰስ የአፍሪካ አገራት ሉዓላዊነት ጋር የማይጣጣም እጅጉን ኋላ የቀረ መሆኑን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ግብፅ ይሄንን አቋም ቀይራ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ጋር እውነተኛ ድርድር ካላደረገች በስተቀር ለወደፊቱ የሚኖራት ስትራቴጂካዊና ምጣኔ ሃብታዊ የትብብር ጥረቶችን እጅጉን የተወሳሰቡ የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም አፍሪካውያን ማናቸውም ችግሮች ሲያጋጥማቸው በራሳቸው መፍታት የሚችሉበት መንገድ መፍጠር እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ።

የአለም ባንክና የአሜሪካ ሚና

የአለም ባንክ አመሰራረቱ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ ሲሆን  ዓላማውም በዋናነት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ለድሃ የአፍሪካ፣ የኤዥያ፣ የላቲንና የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ለትራንስፖት፣ ለሃይል አቅርቦት፣ ለገጠርና ለከተማ መሰረተ ልማት፣ ለት/ትና ጤና መስፋፋትና ተያያዥ የልማት ስራዎች የገንዘብ እና የቴክኒክ እገዛ ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ባንኩ ሃገራት በሚያቀርቡት የልማት ጥያቄ ላይ በመመስረት በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ብድርና ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን መሰረት በማድረግ ለምታቀርባቸው የብድር ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ተግባራዊ ለማድረግና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ከመጀመሪያ አንስቶ ወጥነት ያለው አቋም ስታራምድ ቆይታለች። ለዚህም የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ያስጠበቀ ሳይንሳዊ ትንተና ላይ የተመሰረተና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አቋም በመያዟ በየትኛውም ድርጅት ወይም በማንኛውም ሃገር አሸማጋይነት ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ግልጽ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽን ለማግባባት አሜሪካ ያቀረበችውን ሀሳብ መነሻ በማድረግ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተገኙባቸውን አራት ስብሰባዎች ጨምሮ ከመስከረም 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ አምስት ስብሰባዎች ተደርገዋል።

በእነዚህ የድርድር መድረኮች የታላቁ ህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ የሚመለከቱ ሁሉም ቴክኒካዊ ጉዳዮች በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በሰጡት መግለጫ አስገንዝበዋል።ሶስቱ ሀገራት ሙሌት እና አለቃቀቅን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ መቀራረብ አሳይተዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ሶስቱ ሀገራት በአብዛኛው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልከተዋል።

መፈራረሙን በተመለከተ ግን ዝርዝር ውይይት ስለሚያስፈልግ እንዲቆይ መደረጉን አክለው ገልጸዋል። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ለማስከበር የሚያስችል ውጤታማ ድርድር ማካሄዷን ጠቅሰው በቀረቡ ሰነዶች ላይ የጠራ አቋም ለመያዝ ድርድሩን ያዘገየችው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሶስቱ አገራት ስምምነታቸውን በፊርማ ለማረጋገጥ ፌብሩዋሪ መጨረሻ በዋሽንግተን እንደሚገናኙም ይጠበቃል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን ቴክኒካዊ ቡድኖች እስካሁን ድረስ ያካሄዱዋቸው ጥናቶች ታላቁ የህዳሴ ግድብ በውሃ መጠን ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተፅእኖ እንደማይኖረው የሚያረጋግጡ ቢሆንም ግብፅ በቀዳሚዎቹ ውይይቶች የተስማሙባቸውን መሠረታዊ ሃሳቦች ዋጋ የሚያሳጡ አዳዲስ ፍላጎቶችን በድርድሮቹ ውስጥ እንዲካተት ስታቀርበው በነበረው ሃሳብ እስካሁን ስምምነት ሳይደረስ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የሶስቱ አገራት ድርድር የመጨረሻ መቋጫ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማየት ጥቂት ሳምንታት መታገስ የግድ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም