ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

141

አዲስ አበባ፣ጥር 29/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ትብብር እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል። የከተማዋ ነዋሪ ለእንግዶች የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል

“የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባችን እንግዶቿን ለመቀበል ቀደም ያለ ዝግጅት አድርጋለች፡፡

ከመሪዎቹ ጉባኤ በፊት የሚደረገው የኅብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባም በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት፣ ለአፍሪካ ነጻነት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች፣ አፍሪካውያን አንድ ሆነው ጠንካራ ኅብረት እንዲመሠርቱ የማዕዘን ድንጋዩን ያስቀመጠች ሀገር ነች፡፡

አፍሪካውያን እኅቶቻችንና ወንድሞቻችን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወደ ሌላ ሀገር እንደሚመጡ አይሰማቸውም፡፡ የሚመጡት ወደ ሀገራቸው ነውና፡፡

የሚሰበሰቡት በሀገራቸው ነውና፡፡ የሚመላለሱትም በሕዝባቸው መካከል ነውና፡፡

ይህ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለዘመናት ስታደርጉት የኖራችሁትን ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ከፍ አድርጋችሁ እንድትደግሙት እጠይቃለሁ፡፡

በጉባኤው ምክንያት መንገድ ቢዘጋጋ ለእንግዳ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ቅድሚያ ነው ብለን በጸጋ እንቀበለው፣ አንዳንድ የተለመዱ እንቅስቃሴዎቻችን ቢስተጓጎሉ ‹ቤት ለእንግዳ› ብለን እንለፈው፡፡

በሆቴሎች የተሠማራችሁ አስተናጋጆች የኢትዮጵያ አምባሳደሮች መሆናችሁን አስቡ፤ በመንገድ ላይ የቆማችሁ ፖሊሶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመደባችሁ አስተናጋጆች መሆናችሁን እንዳትዘነጉ፡፡

ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ጉባኤው አዳራሽ የተመደባችሁ ባለሙያዎች የሀገራችሁን ገጽታ የምታሳዩ መስተዋቶች እንደሆናችሁ ስነግራችሁ በአገልግሎታችሁ በመተማመን ነው፡፡

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጉባኤው ፍጻሜ ድረስ መላ ኢትዮጵያውያን በመስተንግዶና ለሚሰጡ መመሪያዎች በመተባበር የሚቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ድል አድራጊ ጸሎታችሁ እንዳይለየን አደራ እላለሁ”፡፡