የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በየአመቱ 1.4 በሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል

76

ጥር 28/2012 (ኢዜአ) በአለም አቀፍ ደረጃ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በየአመቱ 1.4 በሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የአለም የጤና ድርጅት እንደአስታወቀው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሆነው የሴት ልጅ ግርዛት ለከባድ የጤና እክል፣ ለስነ ልቦና ጉዳት ከመዳረጉ በተጨማሪ  ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያጋልጣል፡፡

ድርጅቱ አለም አቀፍ የሴት ልጅ ግርዛት ዜሮ ቶለራንስ ቀንን ባከበረበት ወቅት ባወጣው ሪፖርት የሴት ልጅ ግርዛት በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል በየአመቱ 1.4 በሊዮን ዶላር በአለም አቀፍ ደረጃ ወጪ ይሆናል፡፡

በሪፖርቱ መሰረት አገራት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ ምክንያት የሚከሰተውን የጤና እክል ለመከላከል ለህክምና የሚያወጡት ገንዘብ ከአጠቃለይ አገራዊ ወጪያቸው 10 በመቶውን ይሸፍናል፡፡

በአንዳንድ አገራት ደግሞ 30 በመቶ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡

በዚህ ድረጊት በአለም ላይ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ልጃገረዶች መገረዛቸውን የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፣ ከሚገረዙት አብዛኛዎቹ አስራ አምስትና ከዛ በታች የእድሜ ክልል ወስጥ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ግርዛቱ በሚፈጸምበት ወቅት በሚፈሳቸው ደም በሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች በወሲባዊ ግንኙነት ወቅትና በእርግዝና ጊዜ ለከፍተኛ ህመም ይጋለጣሉ፣ እንዲሁም ለክፉኛ የስነ ልቦና ቀውስ ሰለባ እንደሚሆኑም መረጃው አሳይቷል፡፡