"ፈረስና የሰባት ቤት አገው ..." - ኢዜአ አማርኛ
"ፈረስና የሰባት ቤት አገው ..."

ከመለሰ ይነሱ ባህርዳር (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች አህጉራት የምትለይባቸው የሯሷ የሆኑ አኩሪ መገለጫዎች ያሏት ሀገር ናት። ከሌሎች የአገራችን እሴቶች የዓለም ህዝብ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቅሰውና የሚያውቀው የዓድዋ ድልን ነው። የአገራችን ዜጎች በየሄዱባቸው ሀገራት በኩራት ስለ ኢትዮጵያዊነታቸው እንዲናገሩ በማድረግ ረገድም የአድዋ ድል ታሪክ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። የአድዋ ድል ሲነሳ የአድዋ ፈረሰኞች ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ፈረሰኛ ሲባል ደግሞ በጦር ሜዳ የተሳተፈውን ፈረስና ጋላቢውን ጦረኛ ሰው አካቶ የያዘ ነው። በተለይም ፈረሶች በአድዋ ድል በፈጸሙት ገድል ታላቅ ውለታቸው በመላ ኢትዮጵያዊያን ላይ በሚገባ ባይታወስም በሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ከተመሰረተ ድፍን 80 ዓመታትን አስቆጥሯል ። ማህበሩ በየዓመቱ የምስረታ በዓሉን ማክበሩ ደግሞ የበለጠ እንዲጎላ አድርጎታል።
የዚህ ጽሁፍ መነሻ የአድዋ ድል ለመተረክ ሳይሆን በአድዋ ድል ወቅት የአገው ፈረሰኞች የፈጸሙትን ገድል ለመዘከርና ከድሉ ማግስት የተመሰረተውን “የ ሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር” አመሰራረቱና ምንነቱን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም ማሳወቅ ነው። በመሆኑም ማህበሩ ሰሞኑን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እንጅባራ ከተማ በድምቀት አክብሯል። የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላየ አየነው እንደተናገሩት ማህበሩ በ1932 ዓ.ም በውስን አባላት የተመሰረተ ሲሆን በየጊዜው የአባላቱን ቁጥርና የአከባበር ስነ ስርዓቱን በማሳደግ ዛሬ ላይ ከ50 ሺህ በላይ ፈረሰኛ አባላትን ይዞ በመንቀሳቀስ የሚገኝ አንጋፋና ታሪካዊ ማህበር ነው። የማህበሩ መመስረት ዋና ዓላማም ጣሊያን ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቀላሉ ለማንበርከክ በሞከረችበት ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር በፈረስ ላይ በመፈናጠጥ በጦርና በጎራዴ የፈጸሙትን ገድል ለማስታወስ ነው። ገድሉን ብቻ ሳይሆን የተገኘውን አንጸባራቂና አኩሪ ድል ለመዘከርም ጭምር ነው። ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ወቅት አብዛኛውን ውጊያ በፈረስ ላይ ሆነው እንደ ተፋለሙት ከአባቶቻቸው የሰሙትን ታሪክ በማስታወስ አቶ ጥላዬ ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ በጦር ጀት የሚታገዘውን የጣሊያን ፋሽስት ጦር ድል የነሱት ፈረስን እንደ ትልቅ መዋጊያ መሳሪያነት በመጠቀም እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ኢትዮጵያዊያን ፈረስን የውጊያቸው የጀርባ አጥንት አድርገው ድልን ይቀዳጁ እንጂ በርከታ አርበኞችና ፈረሶች መስዋዕት መሆናቸውም የሚታወስ ነው። ማንም ከሞት በማያመልጥባት በዚች አለም ከሞቴ አሟሟቴን አሳምረው ብለው ለነጻነታቸው ባካሄዱት ተጋድሎ የተሰውት ግን ሞታቸው ተራ ሞት ሳይሆን የክብር ሞት ሆኖ ይታወሳል። የክብር ሞት ማለት ለአገርና ለህዝብ በሚካሄድ ትግል ራስን አሳልፎ መስጠት ነው። አቶ ጥላየ እንደሚሉት ከጦርነቱ የተረፉት የአገው ህዝብ አርበኞች “የፈረስ ውለታው በምን ሁኔታ ይታወስ “ በሚል ከ80 አመት በፊት በየወሩ በ23 ቀን የጊዮርጊስ ዕለት ማህበር በመጠጣትና በየዓመቱ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በዓሉን በመዘከር በታላቅ ድምቀት ማስቀጠል ችለዋል። ማህበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ ከተቋቋመበት አላማ በተጨማሪ የፈረስ ማህበርተኛ አባላትን ትስስር የማጠናከርና በየጊዜው በአባላት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት መተጋገዝን፣ መረዳዳትንና መተባበርን በማጎልበት ሰብአዊነትን ተላብሶ ቀጥሏል ። ማህበሩ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከቀበሌ እስከ ዞን አደረጃጀት በመፍጠር በየአራት አመቱ አስተባባሪ አመራሮችን በመምረጥ የዴሞክራሲ ስርአትን በማሳደግ ረገድም አርአያ የሚሆን ስራን በመስራት ላይ ይገኛል። ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጀት ነጻ የሆነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ አመራሮችን ከመምረጥ በተጨማሪ አባላቱ በየወሩ በሚያዋጡት መዋጮ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ አባላትን የመርዳት ስራም ይከናወንበታል። በአባላቶቹ መካከል መቃቃር ሲፈጠር ደግሞ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በባህላዊ መንገድ አጥፊው እንዲቀጣና ተጎጂው እንዲካስ በማድረግ የእርስ በእርስ ግንኙነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል እያደረገ ይገኛል። ከታሪካዊ ዳራው ባሻገር በርካታ ማህበራዊ መስተጋብሮችን በመወጣት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ የሚገኝ ማህበር ነው። መንግስት የማህበሩን ዓላማ በመረዳት አከባበሩን እንደ ሀገር ማስፋትና የማይዳሰስ ቅርስ ሁኖ በትምህረት፣ሳይንስና ባህል ድርጀት( ዩኒስኮ ) በቅርስነት እንዲመዘገብ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ አቶ ጥላየ በአፅንኦት ተናግረዋል። የማህበሩ ሊቀመንበር እንደሚሉት ፈረስ በአዊ ብሄረሰብ ዘንድ በአድዋ ካስገኘው ድል ባሻገር ማህበረሰቡ የእለት ከእለት ኑሮውን ለመከወን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ለሰው፣ ለእቃና ሌሎች ቁሳቁሶች መጓጓዣነትም ያገለግላል። አርሶ አደሩ የእርሻ ስራውን የሚያከናውነው ፈረስን እንደ በሬ በመጠቀም ነው።ይህ ደግሞ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እምብዛም ያልተለመደ ሲሆን ለአዊ ህዝብ ግን ከበሬ ባልተናነሰ ሁኔታ ፈረስን ለእርሻ አገልግሎት ይውላል ። ይህም ፈረስ በማህበረሰቡ ዘንድ ልዩ ቦታ እንዲኖረው አስችሎታል። ይህ ማህበር በአዊ ብሄረሰብ ዘንድ ታሪካዊና ነባራዊ ውለታዎችን የሚዘክር፣ማህበራዊ ትስስሮችን በማጠናከለርና ዴሞክራሲን በማስፋት ረገድም አርአያ መሆን የሚችል ነው። የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሰት ትኩረት ሰጥተው ሊያጠናክሩት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መለሰ አዳል ናቸው። የማህበሩ አባላት በየዓመቱ የሚያካሂደውን ደማቅ የፈረስ ጉግስ ስነ-ስርዓት ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ ሳይደረግላቸው እዚህ ደረጃ እንዳደረሱት ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እያገኘ በመምጣቱ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በዓሉ ከአድዋ ድል ጋር ተያይዞ የሚከበር በመሆኑ ታሪካዊ ትውፊትነቱን የሚያጎላው ሲሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦችና ለመላው ጥቁር ህዝብ ታላቅ ኩራት ነው። የአለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና ለሃገርም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ይሆናል። በበአሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበከሉላቸው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር ላለፉት ዓመታት ያከናወነው አኩሪ ተግባር የመላ ኢትዮጵያዊያንን ተጋድሎ የሚዘከር ነው ብለዋል። በአሉን በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ባለደርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር በአል የአለም ቀርስ ሁኖ አንዲመዘገብ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ። የበዓሉን አከበባር ሁኔታ፣ አጀማመሩንና አሁን የደረሰበትን እድገት መሰረት ያደረገ ጥናት በምሁራን ማስጠናት ጠቃሚ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህም በዓሉን በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅና እንዲያገኝና የማህበሩን አላማ ለማስፋትና ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረው፤ ይህንን ለማድረግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል። የአገው ህዝብ ለዘመናት ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በማክበር እዚህ ደረጃ በማድረሱ ሊመሰገን ይገባዋል ያሉት ዶክተር ሂሩት አሁን ላይ የአለም ቅርስ ሁኖ እንዲመዘገብ ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ስሜት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
