የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

37

አዲስ አበባ ጥር 28 ቀን 2012 ( ኢዜአ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ ትናንት እንዳስታወቀው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ  ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ይገባሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጀርመን፣ ሴኔጋል፣ አንጎላ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኦማንን ይጎበኛሉ ተብሏል።

ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን የሚጀምሩት የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን ከአራት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ እንደሚደርሱ መግለጫው ያሳያል።

በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር እንደሚገናኙም ተጠቁሟል።

በዚሁ ወቅት የቀጣናውን ሠላምና ደህንነት በጋራ ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረትና  ታሪካዊውን የአገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ መደገፍ በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ እንደሚወያዩም መግለጫው አመልክቷል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ በተጨማሪም ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት ጋር እንደሚገናኙም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም