በሰሜን ሸዋ ዞን 7ኛው ዓመታዊ የስፖርት ውደድር ተጀመረ

84

ደብረብርሃን (ኢዜአ) ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም፥  በሰሜን ሽዋ ዞን በ14 የስፖርት ዓይነቶች ሁለት ሺህ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት 7ኛው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ተጀመረ ።
ትናንት የተጀመረው ዓመታዊው የስፖርት ውድድር ለ12 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከዞኑ 22 ወረዳዎችና 6 የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 2 ሺህ ስፖርተኞች በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል ።

ስፖርት በአካልና በአእምሮ የዳበረ አምራች ኃይል ለማፍራት ካለው ጠቀሜታ አንፃር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክላል ሳህለማሪያም በውድድሩ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል።

ውድድሩ እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ መረብ ኳስና ሌሎችን ጨምሮ በ14 የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ነው ብለዋል ።

የውድድሩ ዓላማ በክልል ደረጃ በሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ዞኑን ወክለው የሚሰለፉ ብቁ ተጫዋቾች ለመምረጥ መሆኑን አቶ ክላል ተናግረዋል ።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ስፖርት ኮሚሽኑ በሃገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክልሉን የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ ነው ብለዋል ።

ሆኖም ግን በየከተሞቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤት ውጤታማ አለመሆኑን ገልፀዋል ።

የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው የሞረትና ጅሩ ወረዳ ህዝብ ከመንግስት ጋር በመተባበር በ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ስታዲዮም ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌነቱ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።