የከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲጠናከሩ ማስቻሉ ተገለጸ

130
አዲስ አበባ፣ጥር 25/2012 ዓ/ም (ኢዜአ) የከተሞች ተቋማዊና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከተሞች የካፒታል ኢንቨስትመንት ፕላን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉ ተገልጿል። የከተሞች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሁለተኛው ዙር የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃ ግብር ውጤትና አፈጻጸም ላይ የመጣውን ለውጥ የሚገመግም አውደ ጥናት ዛሬ አካሂዷል። መርሃ ግብሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በከተሞች የማስፋፊያ አቅምና መሠረተ ልማት እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራ በ44 ከተሞች ሲከናወን ቆይቷል። 556 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት ይህ መርሃ ግብር "ተጠቃሚ ማህበረሰቡን ምን ያህል  ደስተኛ ያደረገና ተጠቃሚነቱስ ምን ያህል ነው" በሚል በዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጥናት ሲደረግበት ቆይቷል። በሚኒስቴሩ የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ፈንድ ሞቢላይዜሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ በአምላኩ አዳሙ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በከተማ ደረጃ የተቀናጀ እቅድ፣ የሃብት አጠቃቀምና የግዥ እንዲሁም የግብር ቅነሳን ያካተተ ሁሉን አቀፍ እቅድ አልነበረም። በመሆኑም መርሃ ግብሩ ከተሞች የካፒታል ኢንቨስትመንት ፕላን ተጠቃሚ እንዲሆኑና የሚያንቀሳቅሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎቻቸውን እንዳገዘ ገልጸዋል። በተለይም ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ መሰረተ ልማቱን በማስፋፋት፣ በስራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በአገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ ከተሞች ለኢንቨስትመንት ምቹ ያልሆኑና ኢንቨስትመንትም መሳብ ያልቻሉ መሆናቸውም ተገልጿል። በመሰረተ ልማት ዙሪያም ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በከተሞች ላይ ከጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የዲች ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አውስተው ይህም አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል። ይሁንና የጥራት ችግር፣ በጊዜ ያለማጠናቀቅና ጠንካራ የስራ አፈጻጸም ስርአት አለመኖር ፕሮግራሙ በሚፈለገው መጠን እንዳይሄድ እንዳደረገው ገልጸዋል። የኮንትራት ማኔጅመንቱ ጠንካራ አለመሆንና የከተማ አስተዳደሮች ትኩረት አናሳ መሆንም ሌላኛው ችግር መሆኑን አክለዋል። ችግሮቹን ለመፍታትና ፕሮግራሙ ውጤታማ ሆኖ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ከክልሎች ጋር በመወያየት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ባለፉት 11 አመታት ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ ከ800 ሺህ በላይ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳዳር የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም