የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠባበቅ ክፍተቶቹን እንዲያርም ተጠየቀ

137
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠባበቅ ላይ ያለበትን ክፍተት በአስቸኳይ እንዲያርም የፌዴራል ዋና ኦዲተር አሳሰበ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን የ2010 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርትን ዛሬ አድምጧል። ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ እንደገለጸው፤ በ2010 በጀት ዓመት የኮሚሽኑን የንብረት አመዘጋገብ፣ አያያዝና አጠባበቅን በንብረት መመሪያ አስተዳደር መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ኦዲት ተደርጓል። በሪፖርቱ እንደተጠቆመው፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በግምጃ ቤትና በተጠቃሚዎች እጅ የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን በቋሚ ንብረትነት ስለመመዝገቡ የሚያሳይ መረጃ የለውም። በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በመጋዘን  የሚገኙ የጦር መሳሪያዎች፣ ስንቅና አልባሳት ቆጠራ ስለመከናወኑ ማስረጃ አለማቅረቡ በሪፖርቱ ተገልጿል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንዳሉት፤ በኦዲት ግኝቱ የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠባበቅ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ግዙፍ ችግር ነው። ''የጦር መሳሪያ  በአግባቡ ተቆጥሮና ተመዝግቦ ካልተያዘ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ስለሚሆን አስቸኳይ መፍትሔ ሊደረግበት ይገባል'' ብለዋል። ''እዚህ አገር ላይ መሳሪያ የሚሸጥ አካል ሳይኖር ለግለሰቦች የጦር መሳሪያ ፈቃድ ይሰጣቸዋል'' ያሉት አቶ ገመቹ፤ ጉዳዩ በትኩረት መታየት እንዳለበት አሳስበዋል። ይህ እንደ ቀላል የማይታይና በፍጥነት መስተካከል እንዳለበት ዋና ኦዲተሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ከጦር መሳሪያ አያያዝና አጠባበቅ በተጨማሪ ከተሰብሳቢና የተከፋይ ሒሳብ እና ከግዥ ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሰራር ሊያበጅለት እንደሚገባ ጠቁመዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አቶ እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው የኦዲት ግኝቱ ካቀረበው ችግሮች ውስጥ 20 በሚሆኑት ላይ የማስተካከያ እርምጃ የወሰደባቸው መሆኑን ጠቁመዋል። የጦር መሳሪያ ቆጠራን በተመለከተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ከጦር መሳሪያ አመዘጋገብ ጋር በተያያዘ ያለውን የህግ ክፍተቶችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወይንሸት ገረሱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጦር መሳሪያ አያያዝ ክፍተቱን በአስቸኳይ እንዲፈታ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም