የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚቀጥለው ሳምንት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

63
ጥር 24/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሴኔጋልንና ጀርመንን እንደሚጎበኙ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ አማራጮች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዲሞክራሲና በጾታ እኩልነት ላይ እንደሚወያዩም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ሲሆን በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር አንደሚመክሩም መረጃው ያሳያል። በአፍሪካ ህብረት 33ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከሚታደሙ የአፍሪካ መሪዎች ጋር ካናዳ ግንኙነቷን በምታጠናክርበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩም ተጠቁሟል። በተለይ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ኢኮኖሚውን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩም ይጠበቃል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የካናዳ አነስተኛ ንግድ የወጪ ንግድ ማስፋፊያና አለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር የሆኑት ወይዘሮ ሜሪ ናግ አብረዋቸው እንደሚመጡ ተገልጿል። በዚህም በሁለቱ አገሮች መካካል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሚያሳድጉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩም ተገልጿል። ኢትዮጵያና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1965 የጀመሩ ሲሆን በቀጠናው ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትበብራውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑ በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም