በፍንዳታው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ግብረ-ኃይል ተቋቋመ

61
አዲስ አበባ ሰኔ19/2010 በመስቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዲቻል በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራ ግብረ- ኃይል ተቋቋመ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ለወሰዷቸው የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ እርምጃዎች ድጋፍና እውቅና ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተጠራው ሰልፍ ላይ በተፈፀመ ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ150 በላይ በሚሆኑ ዜጎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል። የጥቃቱ ተጎጂዎችን መደገፍ እንዲቻልም ግብረ-ኃይል መቋቋሙን ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ለኢዜአ የገለፁት። በከተማዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራ ግብረ-ኃይል በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎችንና የጤና ጥበቃ ሚኒስትርን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአባልነት የያዘ መሆኑንም ኃላፊዋ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በደም ልገሳና በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ዙሪያ ያለውን ስራ እንዲመራ ኃላፊነት እንደተሰጠው አስረድተዋል። ግብረ-ኃይሉ የድጋፍ ፓኬጅ ያዘጋጀ ሲሆን ፓኬጁ በፍንዳታው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አጭርና ጊዜያዊ እንዲሁም ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቤተሰቦችን በዘላቂነት ማቋቋምና መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚያተኩር ነው ወይዘሮ ዳግማዊት የተናገሩት። የድጋፍ ፓኬጁ በቅርቡ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ጸድቆ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ­ጥቃቱ ለተጎዱት ድጋፍ የሚውል የ10 ሚሊዮን ብር መድቧል። ከዚህም ሌላ ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ የሚሹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው የአካውንት ቁጥር 1000250421797 መጠቀም እንደሚችሉም ተመልክቷል። ግብረ-ኃይሉ የተጎዱትን ወገኖች በተመለከተ ከፖሊስና ተጎጂዎቹ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባሉባቸው ሆስፒታሎች የጉዳት መጠንና ደረጃ የተመለከተ መረጃ የማሰባሰብና የማደራጀት ስራ መጀመሩም ተገልጿል። በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሁለት ዜጎች ቤተሰቦች በሚኖሩባቸው ክልሎች ጭምር በመጓዝ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ መረጃ እንደሚሰበሰብም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም