ድሮኖች ለአውሮፕላን የበረራ ደኅንነት እክል እንደይፈጥሩ ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

3884

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 የድሮኖች ያልተገባ እንቅስቃሴ ለአውሮፕላኖች የበረራ ደኅንነት እክል እንደይፈጥሩ ለማስቻል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።

የድሮን ቴክኖሎጂ ለስለላ፣ ለውጊያ፣ ለቅኝት፣ ለፎቶግራፍና ለቪዲዮ ቀረፃ፣ ለመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎቶች አቅርቦትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ይውላል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድሮን ቴክኖሎጂ ለፕሮጀክቶች ምርቃት፣ ለሠርግና ሌሎች ማኅበራዊ ክንዋኔዎች በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል።

ሆኖም ይህ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ካልተጠቀሙበት በአውሮፕላን የበረራ ደህንነት እንዲሁም በሰላምና ደህንነት ላይ ስጋት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሽመልስ ገብረዓብ እንዳሉትም፤የድሮን ያልተገባ እንቅስቃሴ ለተለያዩ ነገሮች እንከን ሊፈጥር ይችላል።

የድሮኖች ያልተገደበ በረራ ለአውሮፕላኖች ደህንነት፣ እንዲሁም ለአገራዊ ደህንት ሥጋት ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።

በቅርቡ በእንግሊዝ አገር ከድሮኖች ያልተገባ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የአውሮፕላኖች በረራ ለሁለት ሰዓታት መስተጓጎሉንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ችግሩ እንዳይፈጠር ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

ለዚህም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የድሮን ቴክኖሎጂ ለግብርና፣ ለመንገድና ሌሎች ልማታዊ ስራዎች ፍቃድ ተሰጥቷቸው ጥቅም ላይ እየዋሉ ቢሆንም በተለይ በከተሞች አካባቢ  ለሠርግና ሌሎች ማኅበራዊ ክንዋኔዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ፍቃድ ያላገኙ ድሮኖች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም በድሮን የሚቀርፁ አካላት በኤርፖርትና በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በምን ያህል ርቀት ነው መብረር ያለባቸው ለሚለው የህግ ማዕቀፍ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ከጉምሩክ፣ ከመከላከያ፣ የደህንነት መስሪያ ቤቶችን ጨምር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

ማንኛውንም በራሪ አካል ወደ አገር እንዲገባና አገልግሎት ላይ እንዲውል ፈቃድ የመስጠት ሥራ በአዋጅ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ነው።

የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ቴክኖሎጂን የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አውሮፓዊያኑ በየካቲት 2002 በአፍጋኒስታን አሸባሪዎችን ለመምታት ተጠቅሞበት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።