35 ሺህ ተማሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል

150

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2012 ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ 35 ሺህ ተማሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን አቋርጠው መውጣታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ትምህርት አቋርጠው የወጡ ተማሪዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ የስድስት ወር የስራ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት አቅርቧል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሚኒስቴሩን ያለፉት ስድስት ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ከህዳር ወር 2012 ዓም ጀምሮ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተፈጠር የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ35ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ለተስተዋለው ችግር ምክንያት ከሆኑት መካከል የተዛቡ የመገናኛ ብዙሃን  ዘገባዎች፣ በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ መሰረተ ልማቶች አለመሟላትና በየአካባቢው የነበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተቋማቱ ውስጥ ችግር በፈጠሩ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የአስተዳዳር ሠራተኞች ላይም ርምጃ መወሰዱን  ነው ፕሮፌሰር ሒሩት ያመለከቱት፡፡

“በዚህም ችግሩ ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ 1 ሺህ 207 መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳዳር ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ ተወስዷል” ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ያለው እንቅስቃሴ ሰላማዊ በመሆኑ  ትምህርታቸውን አቋርጠው የወጡ ተማሪዎችን የመመለስ ሥራ እየተሰራ ነው።

በተከሰተው ችግር ምክንያት የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለማካካስ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ከማድረግ ባለፈ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ መንቀሳቀሱን ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከገቡ 143 ሺህ 842 አዲስ ተማሪዎች መካከል 43 በመቶ  የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አነስተኛ የነበረው የሴቶች የአመራር ተሳተፎን ከፍ ለማድረግ በተሰራው ስራ 26 ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ተደርጓል።

“ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር በተከናወነው ተግባርም 10ሺህ የሚሆኑ ምሩቃንን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

ፕሮፌሰር ሒሩት እንዳሉት፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከዚህ ቀደም የነበረውን ስርዓተ ትምህርት የመከለስ ሥራ ተሰርቷል፡፡

ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ  ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም