የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆችን ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስ እየተሰራ ነው... ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆችን ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስ እየተሰራ ነው... ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ

ሃዋሳ ሰኔ19/2010 በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን ተከስቶ በነበረ ግጭት የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆችን ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ አስታወቁ፡፡ በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ቡድን በገደብ ወረዳና ዲላ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮችን በመጎብኘት ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በወቅቱ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም በዞኖቹ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖችን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር ወደ ቦታቸው ማስመለስ እንደተቻለ አስታውሰዋል፡፡ ግጭቱ መልሶ በማገርሸቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች በድጋሚ ከሚኖሩበት ቀዬ መፈናቀላቸውን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ፣ በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገለፀዋል ። በመጠለያ ጣቢያ እናቶችና ህጻናትን ጨምሮ በአጠቃላይ ለተፈናቃዮች እየቀረበላቸው ያለው የዕለት ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የተፈናቃይ ተወካዮች በበኩላቸው "ለብዙ ዓመታት ከኖርንበት አካባቢ እንድንፈናቀል መደረጉ ተገቢ አይደለም" ሲሉ በዲላ ከተማ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ገልፀዋል። ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተርጫ ወረዳ የተፈናቀሉት አቶ ታሪኩ ሽብሩ በሰጡት አስተያየት " ከኖርንበት አካባቢ እንድንፈናቀል ከተደረገ በኋላ ግለሰቦች ቤት ንብረታችንን አውድመውብናል " ብለዋል ። ተፈጥሮ ለነበረው ግጭት ምክንያት የሆኑ አመራሮችም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። ሌላው ተፈናቃይ አቶ ሳሙኤል ኪቤ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የሁለቱ የክልልና ዞን አመራሮች ባሉበት በጎንዶሮ እርቀ ሰላም ተደርጎ ወደ ቤታቸው ተመልሰው እንደነበር አስታውሰዋል። ግጭቱ መልሶ በማገርሸቱ ዳግም መፈናቀላቸውን የገለፁት አቶ ታሪኩ በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውን ገልፀዋል ። በጉብኝቱና በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ከተፈናቃዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። "በእነዚህ ሁለት ህዝቦች መካከል በሚፈጠር ግጭት ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ አካላት ተጠቃሚ መሆን እንደማይችሉ አውቀው አርፈው ሊቀመጡ ይገባል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለተፈጠረው ችግር ምክንያት የሆኑትን በመለየት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል አደጋ መከላከልና ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ከተፈናቃዮች መካከል የሚያጠቡ እናቶችና ህጻናት መኖራቸውን ገልጸዋል ። "ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው የዕለት እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ተረድተናል" ያሉት ኮሚሽነሩ አቅርቦቱን ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በገደብ ወረዳና ዲላ ከተማ የተጠለሉ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ቁጥር 642 ሺህ መድረሱ ታውቋል፡፡