መኢአድ በመስቀል አደባባይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አወገዘ

112
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በተጠራው  የድጋፍ ሰልፍ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አወገዘ። ፓርቲው በጉዳቱ ሕይወታቸውን ላጡና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል። ጥቃቱን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው  "የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አካሄድ ያልጣማቸው የጥፋት ኃይሎች ብዙ መሰናክሎች ለመፍጠር እየጣሩ ነው" ያለው ፓርቲው። በመስቀል አደባባይ የታየው የሽብርተኝነት አባዜ የተጠናወታቸው አካላት የፈጸሙት የአሸባሪዎች ድርጊት መኢአድ በጽኑ እንደሚያወግዘው የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ ተናግረዋል። "የግል ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ሽብርተኝነትን ማስፋፋት ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር ነው" ሲሉም ድርጊቱን  አውግዞታል። መንግስት የወንጀሉን ፈጻሚዎችና የድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ አካላትን ተከታትሎ በመያዝ ለፍርድ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንድያገኙናለሟች ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የማጽናኛና የማበረታቻ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቋል። እንዲሁም ለአንድነትና ለፍቅር ሲሉ ሕይወታቸው  ለከፈሉ ወገኖች የሀዘን ቀን እንዲታወጅና ሰኔ 16 ቀን "የአንድነት ቀን ተብሎ ብሄራዊ በዓል" ሆኖ እንዲታወጅ ሲል መኢአድ ጠይቋል። ሰኔ 16 ቀን 2019 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ  ላመጧቸው ለውጦች ለመደገፍና ለማመስገን በተካሄደው ሰልፍ የቦንብ  ጥቃት ተከስቶ ለሁለት ሰዎች ህይወት ማለፍና ከ150 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱ አይዘነጋም።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም