የዓለም የጤና ድርጅት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያደርግ ነው

81
ጥር 21 ቀን 2012 ዓ/ም ( ኢዜአ) የዓለም የጤና ድርጅት ኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ዛሬ አስቸኳይ ስብስባ ያደርጋል። ድርጅቱ በታህሳስ ወር ያቋቋመው የኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ ኮሚቴ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ስብሰባውን እንደሚያደርግ የዓለም የጤና ድርጅት በድረ ገጹ አስፍሯል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመሩት ስብሰባ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚካሄድ ነው። የድርጅቱ የጤና ባለሙያዎች ለዶክተር ቴዎድሮስ የኮሮና ቫይረስን አሁን ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻና ምክረ ሀሳብ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ከውይይቱ በኋላ የዓለም የጤና ድርጅት የሚያሳልፈውን ውሳኔ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች ያቀረቡት ምክረ ሀሳብም ይፋ እንደሚሆንም ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እስካሁን በቻይና 170 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ 7 ሺህ 717 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከቻይና ውጪ 17 አገሮች የኮሮና ቫይረስ በአገራቸው መታየቱን አረጋግጠዋል። አውስትራሊያ፣ ካምቦዲያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ማሌዢያ፣ ኔፓል፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስሪላንካ፣ ታይዋን፣ ታይላንድ፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ቬትናም ቫይረሱ የተገኘባቸው አገሮች ናቸው። በ17ቱ አገሮች ውስጥ 106 በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች ቢገኙም በበሽታው ህልፈተ ህይወት ያጋጠማቸው ሰዎች የሉም። ቻይና ቫይረሱን ለመከላከል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በክትትል ማቆያ ውስጥ ህክምና እያደረገች ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ገደብ ጥላለች። በተጨማሪም የቫይረሱ መዛመት ለመከላከል አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በስፋት እያመረተች ትገኛለች። በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች ተለይተው በማቆያ ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው። ከአራቱ ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ቫይረሱ በመጀመሪያ ከታየባት የቻይና ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ የመጡና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው የተጠረጠሩ ናቸው። በአገር ውስጥ በተደረገ ምርመራ ነጻ መሆናቸው ቢረጋገጥም ሙሉ ለሙሉ ነጻ ስለመሆናቸው ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የደማቸው ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም