የኢትዮ-ጀርመን የባለሙያዎች የምክክር መድረክ ተካሄደ

1352

ጥር 21/2012 (ኢዜአ) ጥር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ጀርመን የባለሙያዎች የምክክር መድረክ በተካሄደው ውይይት የተደረሱ ስምምነቶችን በሚመለከት የተዘጋጀውን ቃለ ጉባኤ በመፈራረም መጠናቀቁ ተገልጿ።

ሁለቱ ወገኖች በሰኔ ወር 2011 ዓም በበርሊን በተፈራረሙት የጋራ ኮሚሽን ስምምነት መሰረት እና የሁለቱ አገሮች የጋራ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የትብብር መስኮችን ማስጀመር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የባለሙያዎች የምክክር መድረክ ሁለቱ አገሮች በውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ጉዳዮች፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በማህበራዊ ልማት፣ በሰዎች ዝውውር፣ በኢነርጅ እና አየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ መድረኮች የሚያደርጓቸውን ትብብሮች ለማጠናከር በሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮች በመምከር እና የተዘጋጀውን ቃለ ጉባኤ በመፈራረም ተጠናቋል።

በምክክር መድረኩ ከአትዮጵያ ከተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶች የተውጣጡ 35 ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፡ ከጀርመን በኩል ደግመ 43 ባለሙያዎች ተሳፈዋል።

የምክክር መድረኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ ጥር 19 ቀን 2012 ዓም በይፋ የተከፈተ ሲሆን፤ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ውይይት በኢትዮጵያ በኩል በአውሮፓ ጉዳዮች ዳ/ጄኔራል አቶ ምህረታብ ሙሉጌታ ተመርቷል። በጀርመን በኩል ደግሞ የጀርመን ፌደራል ውጭ ጉዳይ ቢሮ የሰሃራ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ሮበርት ዶልገር መርተውታል።

ኢትዮጵያና ጀርመን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት በ1897 ዓም መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

(ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)