የኖብል ኮሮና ቫይረስ በመላው ቻይና መሰራጨቱ ተነገረ

64

ኢዜአ ጥር 21/2012 በቻይና ውሃን  ግዛት  የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአሁኑ ሰዓት በመላው   ቻይና መሰራጨቱና  የሟቾች   ቁጥርም 170 መድረሱ ተገለፀ።

የቻይና የጤና ባለስልጣናት እንደገለጡት አሁን ላይ በሀገሪቱ 7 ሺህ 711 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

ቫይረሱ ከቻይና በተጨማሪ  በ16 የአለም ሀገራት መዛመቱ ተገልጿል።

ኮሮና ቫይረስ የከፋ የመተንፈሻ አካላት ህመምን በማስከተል እስከ ሞት የሚያደርስ ሲሆን በተለይም በሽታው ቀደም ሲል ህመም በነበረባቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ እንደሚጸና ባለሙያዎች ይናገራሉ። እስካሁን ድረስ ቻይና ውስጥ በበሽታው መያዛቸውና መሞታቸው የተረጋገጠው አብዛኞቹ ሰዎች ሁቤይ የምትባለው ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው እና ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የዉሃን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል። በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ያሉ ሰዎች እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን ቻይና የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት በግዛቶቿ ውስጥ በርካታ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን ጥላለች።

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት  ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በሽታውን በተመለከተ በትናንትው እለት ባደረጉት ንግግር "በሽታው ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ አሳስቦናል" ብለዋል፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አክለውም "ከቻይና ውጪ ያለው የቫይረሱ ስርጭት በአንፃራዊነት ትንሽ ቢሆንም ከፍተኛ ወረርሽኝ ሊያመጣ የሚችልበት ዕድል አለ" ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በዛሬው እለት ተሰብስቦ በበሽታው  ላይ በመምከር በሽታው ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ስለመሆኑና አለመሆኑ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።

(ቢቢሲ)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም