በአካባቢው የተፈጸመው እገታ የብሔር መልክ እንደሌለውም ተገልጿል

103
አዲስ አበባ ኢዜአ፤ጥር 20/2012  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የፌዴራል ፖሊስና የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ስለታገቱት ተማሪዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የጠቅላይ ሚስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አንፊሎ ወረዳ ውስጥ ሱዲ በተባለ ስፍራ ህዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ታግተው ተወስደዋል። የአካበቢው የሚንቀሳቀሰው የጸጥታ ኃይልም የእገታ ሪፖርቱ እንደደረሰው ባካሄደው አሰሳ 21 የሚሆኑትን ወዲያው በማስለቀቅ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ማድረጉን ነው የተናገሩት። መንግስትም ይህን የተመለከተ መረጃ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ማድረጉን በማስታወስ። በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር በመሸሽ ላይ የነበሩ ሌሎች ተጨማሪ 19 ሰዎች መታገታቸውን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ ከመካከላቸው 14ቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን አመልክተዋል። የቀሪዎቹ አምስት ታጋቾች ስም ዝርዝር ከዩኒቨርሲቲው መረጃ  ቋት ውስጥ ሊገኝ አለመቻሉን ገልጸዋል። በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 800 ያህሉ ግቢውን ለቀው መውጣታቸውንም  አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው በአካባቢው በትጥቅ በመታገዝ ህዝብን የሚያሸብር ቡድን መኖሩን ጠቁመው፤ መንግስት በወሰደው እርምጃ አብዛኛው አካበቢ ወደ ሰላም እየተመለሰ ነው ብለዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ጥቂት ህገ-ወጥ አከላት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የአካባቢውን ሰላም እያወኩ ይገኛሉ ነው ያሉት። መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ሶስት ቡድኖችን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ኮሞሽነር ጀኔራሉ አውስተዋል። ነገር ግን በተማሪዎቹ ላይ የደረሰ የአካል ጉዳት ስለመኖሩ የተገኘ መረጃ እንደሌለም ገልጸዋል። የሚገኙ አዳዲስ መረጃዎች ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ በየጊዜው ለህዝብ ይፋ እንደሚሆኑ በመጠቆም 'በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ህገ-ወጥ ቡድን ከተማሪዎች በተጨማሪ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ እገታ እና እንግልት እየፈጸመ ነው" ያሉት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ  ናቸው። ይህም እገታውና ህገወጥ ድርጊቱ  የብሔር መልክ እንደሌለው በግልጽ ያሳያል ብለዋል። የችግሩ ቁልፍ ጉዳይ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ችግር በመፍጠር እንደ ሃገር የተጀመረውን ለውጥ እንዳይሳካ መሰራት መሆኑን በማብራራት። መንግስት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት አስቀድሞ የቤት ስራውን ባይሰራ ኖሮ የጉዳት መጠኑ እጅጉን አስከፊ ይሆን እንደነበርም አውስተዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ተረጋግተው የመማር ማስተማር ሂደታቸውን አንዲቀጥሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራው ያለውን ስራ እንደሚቀጥልም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም