በቡኖ በደሌ ዞን 264 ሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ተያዘ

99
መቱ ኢዜአ ፤ጥር 20 ቀን 2012 ዓም በቡኖ በደሌ ዞን በተለያዩ ጊዜያት በተደረገው ቁጥጥር 264 ሰዎች በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ መገኘታቸውን የዞኑ ትራንስፖርት ባለሰልጣን አስታወቀ:: የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ አቤቤ እንዳሉት በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት 39 የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል ። ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ27 አደጋዎች ብልጫ አሳይቷል ብለዋል ። በተለያዩ ጊዜያት በደረሰው የትራፊክ አደጋ 20 ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ በ32 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት የአካል ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል:: ለአደጋው እየጨመረ መምጣት ዋናው ምክንያት ከመጠን በላይ መጫንና ትክክለኛ መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ማሽከርከር እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል። በአካባቢው የተገነቡ የአስፋልት መንገዶችም የፍጥነት መቆጣጠርያ መሳሪያ ስላልተገጠመላቸው  ከተገቢው ፍጥነት በላይ በማሽከርከር ለአደጋዎች መበራከት ተጨማሪ  ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል ። ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመተባበር ስምሪቶችንና የሌሊት ጉዞን የመቆጣጠርና ትርፍ ጭነትን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ። በዞኑ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የትራፊክ ዲቪዥን ሀላፊ ኢንስፔክተር በሀይሉ ገዛኸኝ በበኩላቸው በዞኑ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል የተሽከርካሪ ደህንነትና በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ያተኮረ የተቀናጀ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። በዚህ አመት በተለያዩ ጊዜያት በተደረገው ፍተሻ በሐሰተኛ መንጃ ፈቃዶች ሲያስሽከረክሩ የነበሩ 264 ሰዎች ተይዘው በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን ነው የገለጹት ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም