በአማራ ክልል ኮንትሮባንድን የመከላከሉ ስራ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ

65

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 19/2012 በአማራ ክልል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ገለጸ። በቅርንጫፍ የደንበኞች ትምህርትና ድጋፍ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፋ አራጋው ለኢዜአ እንዳሉት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በተደራጀ አግባብ ለመግታት ጥረት እየተደረገ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ስድስት  ኬላዎች በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል ከ33 ሚሊዮን 500ሺህ ብር ግምት ያላቸው እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም አንድ ሚሊዮን 400ሺህ ብር  ግምት ያላቸው ደግሞ ከሃገር ለማስወጣት ሲሞከር በቁጥጥር ስራ መዋሉን አመልክተዋል።

ከተያዙት እቃዎችም አልባሳት፣ ሲጋራ ፣ኮስሞቲክስና ሌሎች ሸቀጦችም ይገኙበታል።

 ህገ ወጥ የሆኑ 34 ሺህ 104 የጦር መሳሪያዎች ፣ወንጀል ሲፈጸምባቸው የነበሩ 79 ተሽከርካሪዎችና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ይመራሉ ተብለው የተጠረጠሩ 105 ሰዎች ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ አስተባባሪው አስታውቀዋል።

ህገ-ወጥ እንቅስቃሴው ሰፊ የነበረ ቢሆንም የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል ከኮሚሽኑ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ጥምረት ማክሸፍ መቻሉን አብራርተዋል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሃገርን ልማትና እድገት የሚጎዳ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን በመረዳት ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ አስተባባሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም