ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለስልጣናት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠትና ለምርመራ እንደማይተባበሩት ገለጸ

314

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የመንግስት ባለስልጣናት በተለይ የክልል አካላት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠትም ይሁን ለምርመራ ተባባሪ አለመሆናቸው ለስራው እንቅፋት እንደሆነበት አስታውቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያለበትን ህግ የማስከበር ክፍተት እንዲፈታ ማሳሰቢያ ሰጥቶታል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ አመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት ያከሄደ ሲሆን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የስራ አፈፃፀም ሪፖርትን ገምግሟል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሪፖርቱ እንዳመለከተው በሙስና ወንጀል የተመዘበረ የህዝብና የመንግስት ሃብት ከፍርድ ቤት ክርክር ውጭ አስመልሷል።

በዚህም 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ከገንዘብ ቅጣት፣ ሂሳብ እንዲወራረድ በማድረግ፣ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ በድርድርና በህጋዊ አማራጭ 511 ሚሊዮን 696 ሺህ 751 በር ገቢ እንዲሆን ማድረጉን ገልጿል።

ይሁን እንጂ በአገሪቱ ብጥብጥና ሁከትን በማስነሳት፣ በሙስናና ሌሎች ወንጀሎች ለምርመራና ለህግ ከሚፈለጉ ሶስት ሺህ ያህል ተጠርጣሪዎች መካከል በቁጥጥር ስር ማዋል የቻለው 1 ሺህ 404 ብቻ ነው።

በመሆኑ በብጥብጥና ሁከት ማስነሳት፣ በሙስናና ሌሎች ወንጀሎች የሚፈለጉ 1 ሺህ 596 ያህል ተጠርጣሪዎች አልተያዙም።

በተለያዩ የሙስና፣ የሽብርና መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች በአገር ውስጥ እየኖሩ ለህግ አለመቅረባቸውን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ቀርቧል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ችግር የፈጠረው የክልል መንግስታትና ህግ አስከባሪዎች ከፌዴራል መንግስት ጋር የመተባበርና የህግ ግዴታቸውን አለመወጣት መሆኑን ተናግረዋል።

”ወንጀል ፈጻሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ የክልል መንግስታትና ህግ አስከባሪዎች ከፌዴራል መንግስት ጋር ተገቢውን ትብብር አለማድረግና ግዴታቸውን አለመወጣትና በተለያየ እርከን ያሉ የተወሰኑ አመራሮች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የወንጀል ተሳታፊ መሆናቸው ህግ የማስከበር ስራውን ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ዝውውር፣ የሃሰት ወሬዎችና የጥላቻ ንግግር መስፋፋት የህግ የበላይነትን የመፈታተን አዝማሚያ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

እነዚህን ወንጀሎች በብቃት ለመመርመር የዳበረና ዘመናዊ የምርመራ ክህሎት ማነስም አንዱ ክፍተት መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጠቅሰዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ባነሱት ጥያቄ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች የህግ ሂደታቸው በወቅቱ አልቆ ውሳኔው አለመታወቁ፣ እስካሁን ድረስ ጨለማ ቤት መታሰርና ግርፋት አለ የሚሉ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጨለማ ቤት መታሰርና ግርፋትን በተመለከተ የሚወራው ከእውነት የራቀ ነው ሲሉም መልሰዋል።

የታራሚዎች አያያዝና ሰብአዊ መብትን በተመለከተም እስካሁን የጨለማ ቤትና ግርፋት አለ የሚል ቅሬታ መኖሩን ከምክር ቤት የተነሳ ሲሆን ይህ ለፖለቲካ ፍጆታ የዋለ ፕሮፖጋንዳ እንጂ በመሬት ላይ የሌለ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲ ከሚፈጠሩ ግጭቶች በተለይም በታገቱት ተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ግልፅ የሆነ መረጃ አለመቅረቡን ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር ያለውን ተሳትፎም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከፖሊስና ከክልሉ የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ጉዳዩን እያጣራ ስለሆነ እንዳለቀ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በማጠቃለያው የህዝብንና የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ፣ ህግን ከማስከበርና ፍትህን ከመስጠት አኳያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት የቤት ስራ ሰጥቶታል።