የኢትዮ-ጀርመን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የባለሙያች የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

61

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2012 የመጀመሪያው የኢትዮ-ጀርመን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የባለሙያች የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው የመጀመሪያው የኢትዮ-ጀርመን የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የባለሙያዎች የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከ100 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረና በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ጀርመን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ከመፍጠር ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ሁለቱ አገሮች ካላቸው የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት አንጻር ግን የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም።

ሆኖም የጋራ መድረኩ ውስንነቶችን በመለየት ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍ ያለ ሚና እንዳለው አምባሳደር ማህሌት ጠቅሰዋል።

የሁለቱን አገሮች ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በተሻለ በማጠናከር ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ለሚካሄደው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ የመፍትሔ ሃሳቦች ለማቅረብም ያሰግዛል ብለዋል።

የጀርመን የባለሙያዎች ቡድን ተጠሪ ፌዴራል ውጭ ጉዳይ ቢሮ የሰሃራ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሮበርት ዶልግረ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያም ዋነኛዋ የጀርመን አጋር መሆኗን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነቶች ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸውም ሮበርት ዶልግረ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የተጀመረው ውይይት በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ትብብር፣ በስደተኞች ዙሪያ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እና በየአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኩራል።

በውይይቱ ላይ 35 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እና 43 የጀርመን ልኡክ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም