በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ600 ሺህ በላይ የገጠር ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል

108

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19/2012 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ከ600 ሺህ በላይ የገጠር ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በዚህ በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን 700 ሺህ የገጠር ወጣቶች ስራ ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን እስካሁን 670 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አብዛኞቹ ወጣቶች በእንስሳትና በእፅዋት ግብር ና ስራዎች መሰማራታቸውን የሚኒስቴሩ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየተሰሩ ያሉ የገጠር ሥራ ፈጠራ ክንውን መልካም  እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

እስከታችኛው እርከን ድረስ በትኩረትና በቅንጅት በመስራት እንዲሁም የስልጠናና ብድር አገልግሎቶችን በወቅቱ በመስጠት ውጤታማ ስራ እያስመዘገቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀሩት ክልሎች ስራው በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅትና በትኩረት አለመስራት፣ የመሬትና የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት እንዲሁም ግብዓቶች በወቅቱ አለመሟላት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በየአካባቢው ያለውን ዕድል አለመጠቀም፣ ዘመናዊ አሠራር አለመከተል፣ የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ ግብርናን እንደ አዋጪ የሥራ ዘርፍ አለማየት ና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የአንድ ማዕከል አገልግሎት አለመኖር ችግሮች እንዳሉም አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ ትኩረት ከሚሰጣቸው የገጠር ግብርና ዘርፎች መካከል የእንስሳት ዕርባታ ዘርፍ ዶሮ እርባታ፣ ከብት ማድለብ እንዲሁም የአትክልትና ፍርራፍሬ ልማት ሥራዎች እየተሰራባቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

የተማረና ወጣት የሰው ኃይል ዕድልን መጠቀም፣ ዘመናዊ አስተሳሰብና አሠራር መከተል እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀምና በቅንጅት በመስራት የአገሪቷን ግብርና በማሳደግ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል ዳይሬከተሩ።

የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራው የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በአገሪቷ ያለውን የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምና የኑሮ ውድነት ሊፈቱ የሚችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

በግብርና ላይ እየተከናወነ ባለው የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ መሆኑንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በሁሉም ክልሎች በትብብር እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ለተገነቡ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት ለ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ መፍጠሩን ገልጾ ክንውኑ ግን ከተያዘው ዕቅድ ያነሰ እንደሆነ ጠቁሟል።

በአገሪቷ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ስጋቶች ለዜጎች በርካታ ስራ እንዳይፈጠር ካደረጉ እንቅፋቶች መካከል ነው።

የሥራ ዕድል ከተፈጠረባቸው ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እንዲሁም የግልና የመንግሥት አገልግሎት ዘርፎች ትልቁን ቦታ እንደሚይዙ ኮሚሽኑ የስድስት ወር ግምገማውን በመቀሌ ሲያካሂድ ገልጾታል።

በኢትዮጵያ 36 ሚሊዮን ሄክታር ለእርሻ ልማት የሚውል መሬት ቢኖርም እየለማ ያለው ከ16 ሚሊዮን ሄክታር እንደማይዘል መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም