በጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ

54
ጋምቤላ፣ ጥር 19/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ከ17 የጦር መሳሪዎች ጋር ትናንት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። በፌዴራል ፖሊስ የምራዕብ ዳይሬክቶሬት አንደኛ ዲቪዥን ሶስተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ተረፈ በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሊውሉ የቻሉት በአንድ መኖሪያ ቤት የጦር መሳሪያዎችን ደብቀው በመገኘታቸው ነው። ከተያዙት የጦር መሳያዎች መካከል 11 ታጣፊ ቀሪዎቹ ደግሞ ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች  ናቸው። በአሁኑ ወቅት በግለሰቦቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ያመለከቱት ኢንስፔክተር ተረፈ  "የምርመራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት የሚላክ ይሆናል" ብለዋል። በክልሉ እየተስፋፋ የመጣው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት ከክልሉ የጸጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ። እንደ ኢንስፔክተሩ ገለፃ ትናንት የታዙትን ጨምሮ ባለፈው ስድስት ወራት  28 የተለያዩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪዋችና ከ600 በላይ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም