የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት “ጠንቃቃ አሽከርካሪዎች” ያላቸውን 28 የአውቶብስ ካፒቴኖች ሜዳሊያ ሸለመ

215

አዲስ  አበባ (አዜአ) ጥር 18/2012 የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ ሳያደርሱ በጥንቃቄ ሲያሽከረክሩ የነበሩ 28 የአውቶብስ ካፒቴኖችን የነሐስ ሜዳሊያና ሰርተፍኬት ሽለመ።

የድርጅቱ ዋና  ስራ አስኪያጅ አቶ ጎይቶም ሃይሉ  በሽልማት ስነ ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት የትራፊክ ህግን በማክበር በጥንቃቄ የሚያሽከረክሩ የባስ ካፒቴኖችን መሸለምና ማበረታታት ይገባል።

“ጠንቃቃ” ሹፌሮች ሲሸለሙ በቀጣይም ይሄው ጥረታቸው እንዲቀጥልና ሌሎች አሽከርካሪዎችም ከነሱ እንዲማሩ ያግዛል ብለዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል ካፒቴን ይታገስ  ታደለ  እንደገለጸው ለትራፊክ አደጋ መባባስ ዋናው ምክንያት የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ ነው።

በመሆኑም ጠንቃቃ አሽከርካሪዎችን መሸለምና ማበረታታት ሌሎችም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ያደርጋል ብለዋል።

ላለፉት ሁለት አመታት የባስ ካፒቴን ሆኜ ሳሽከረክር ያደረስኩት አንዳችም አደጋ ባለመኖሩ ተሸልሜአለሁ ያለችን ደግሞ ካፒቴን ማርታ ጌታቸው ነች።

እራሴንና ሌሎችን ከትራፊክ  አደጋ ለመታደግ በትዕግስትና በጥንቃቄ ለማሽከርከር በአርአያነቴን ለመቀጠል ሽልማቱ ያበረታታኛልም ብላለች።

የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ ተቋም ነው።