የአደረጃጀት ውሳኔው ችግሮቻቸውን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

74
ጥር 18/2012 (ኢዜአ)  ባሌ በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ መወሰኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻቸውን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ የምስራቅ ባሌ ዞን ምስረታ ይፋ ሆኗል። በዚህ ወቅት ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት የአደረጃጀት ውሳኔው መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው ለማግኘት ያስችላቸዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል ሀጂ ዩሱፍ መህዲ በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸው   በዞን ደረጃ  እንዲደራጅ የዘመናት ጥያቄያቸው  እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በተለይ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ከዚህ በፊት መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው ለማግኘት ሲቸገር መቆየቱን አውስተዋል። ውሳኔው መንግስት የህዝቦችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ማሳያ መሆኑንም ሀጂ ዩሱፍ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች የተሟላ  የመሰረተ ልማት ባለመኖሩ ወደ ባሌ ሮቤ ለመምጣት አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የዞኑ ነዋሪ ሼህ አህመድሳሊህ ከዲር ናቸው፡፡ መንግስት የአካባቢው ማህበረሰብ ለዘመናት ያነሳ የነበረውን ችግር በማጤን ለአስተዳደር እንዲያመች የአደረጃጀት ውሳኔ ማሳለፉ ለህዝቡ የሰጠን ትኩረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳመለከቱት አደረጃጀት ውሳኔው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻቸውን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የመሰረተ ልማቶት ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ እንዲያገኝ ትኩረት እንዲሰጥም ጠቁመዋል ፡፡ የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው “የባሌን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል። የአደረጃጀት ውሳኔው ህዝቡ ከመንግስት የሚፈልገውን አገልግሎት በአቅራቢያው በፍጥነት እንዲያገኝና  የተጓደሉ መሰረተ ልማቶችም እንዲሟሉ የሚያመች መሆኑን ተናግረዋል። “ውሳኔው የክልሉ መንግስት የሚያስተዳድረውን ህዝብ የልብ ትርታ በማዳመጥ ጥያቄውን ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው “ ብለዋል። ህዝቡ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርስ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ከመንግስት ጎን እንዲቆምም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ጎሳ ፋይሳ እንደገለጹት መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ “የባሌ አካባቢ መንግስታዊ አገልግሎትን ህዝቡ በአቅራቢው እንዲገኝ በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ መደረጉ የዚሁ ጥረት አካል ነው “ብሏል፡፡ መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እንዲፈታ ብሎም ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን መተባበርና በጋራ መስራት እንደሚስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ለአካባቢው ህዝብ ልማትና እድገት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ የቀረበለትን ጥናት መነሻ በማድረግ ባሌን ምስራቅ እና ምዕራብ ሆኖ በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ መወሰኑን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል። በውሳኔው መሠረትም የምዕራብ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ ሲሆን የምስራቁ ደግሞ ጊኒር ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም