በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው

57
አዲስ አበባ ጥር 18/2012 (ኢዜአ) በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በቻይና በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በግልና በመንግስት የነጻ የትምህርት እድል ተሰጥቷቸው የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ ቻይና የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ ይገኛል። እስከ ዛሬ ድረስ ባለው መረጃ በቻይና በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ኤምባሲው ማረጋገጡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በተለይ የኮሮና ቫይረስ መነሻ በሆነችው በቻይና ሁቤ ግዛት ውስጥ ውሃን ከተማ ከ300 በላይ ኢትዮጵያዊያን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። ተማሪዎቹ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኤምባሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመልክቷል። በቻይና የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቲቤት ክፍለ ሃገር ውጭ በታይዋን፣ ሆንግ ሆንግና ማካኦን ጨምሮ በሁሉም የቻይና ግዛቶች እንዲሁም ከቻይና ውጭ በአሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ኔፓልና ማሌዥያ መከሰቱ ተረጋግጧል። እስካሁን ባለው መረጃ 2 ሺህ 744 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ከነዚህም ውስጥ 81 ሰዎች በዚሁ ቫይረስ መሞታቸውን የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። 'ኖቭል ኮሮና 2019' የተባለ የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በሰጡት መግለጫ ”ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አኳያ ቫይረሱ የሚገባባቸው ዕድሎች ሰፊ ናቸው” ብለውም ነበር።ከዚህ አኳያ ከቻይና የሚመጡ ተሳፋሪዎች ላይ ምርመራ መደረግ መጀመሩን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቮላን ጨምሮ ተመሳሳይ ቫይረሶች ላይ ቅድመ ምርመራ ለማድረግ የተዘጋጁ ቦታዎች ለዚሁ አገልግሎት እንደሚውሉ ዶክተር ኤባ ገልጸዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ለይቶ የማቆያ ስፍራ መዘጋጀቱንና የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ጥቁር አንበሳና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች በጊዜያዊነት የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ ሆነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም