በትግራይ ክልል ከኤክስፖርትና ከአገልግሎቶች 110 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

257

ጥር 17 ቀን 2012 መቀሌ (ኢዜአ ) በትግራይ ክልል ባለፉት 6 ወራት ለውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶችና ከአገልግሎቶች ከ110 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ ተገለጸ።

   የውጭ ምንዛሪ ገቢው የተገኘው  ባለፉት ስድስት ወራት  ከክልሉ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶችና ከቱሪዝም አገልግሎት መሆኑን  የየዘርፉ የስራ ሀላፊዎች ገለፀዋል ።

የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንትና ኤክስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ  የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ  ውጤቶች 49 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ገቢ ተገኝቷል ።

ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 37 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከሰሊጥ ፣ አትክልትና ፍሬፍሬ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በትግራይ ደቡባዊ ዞን ራያ አካባቢ የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በአውሮፓ ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት እያደገ  ከመምጣቱ በተጨማሪ በሰሊጥ ምርቶች ብቻ ተወስኖ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት አሁን እየሰፋ በመምጣቱ ነው ብለዋል ።

በክልሉ የሚገኙ  ታሪካዊ ቦታዎችና የቱሪዝም መስህቦች ለማየት ከ45 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች ትግራይን መጎብኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ  የገበያ ማስተዋወቅ ባለሙያ አቶ ዮናስ ታደለ ናቸው።

የውጭ ጎብኚዎች በቆይታቸው ወቅት ለተጠቀሙባቸው አገልግሎቶች 62 ነጥብ 7 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ክልሉ ኢኮኖሚ  መግባቱን አስረድተዋል ።

ጎብኚዎቹ የቆይታ ጊዜአቸውን ለመጨመር የሚፈልጉዋቸውን አገልግሎቶች በማሟላትና የመዳረሻ ቦታዎች ለማብዛት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክና የኢሮፕ መልከ አምድራዊ አቀማመጥ የመሳሰሉት አዳዲስ መዳረሻዎች ለገቢው ማደግ እገዛ ማድረጋቸውንም አቶ ዮናስ ገልፀዋል ።

በክልሉ ያለው ሰላም፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መሻሻል  ፣የሆቴሎችና ሎጆች መስፋፋትና ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ማደግ በቱሪስት ፍሰት ላይ ገንቢ ሚና እንደተጫወቱ ከአቶ ዮናስ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል ።

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የቱሪስት ስፍራዎች  ለማስተዋወቅ የበኩላቸው ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ደግሞ ለዘርፉ ማደግ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል ።

በመቐለ ከተማ የዘመናዊ ሆቴል ባለቤት የሆኑት ዶክተር ብስራት ገብረእግዚአብሄር በሰጡት አስተያየት ሆቴላቸው በሚሰጠው የተሟላ  አገልግሎት የውጭ ጎቢኚዎች በብዛት እንዲያርፉ በማድረግ  ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን  ተናግረዋል።