በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ ወደ ልማት ለመቀየር እንረባረብ ---አቶ ርስቱ ይርዳው

69
ዲላ ኢዜአ ጥር 16/2012 ዓ/ም  በደቡብ ክልል ያለውን ምቹ ሁኔታ ወደ ልማት ለመቀየር እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንረባረብ ይገባል ሲሉ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ ። የጌዴኦ ዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓል በዲላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት በክልሉ ባህልና ቋንቋን ከማሳደግ አንጻር ያለውን ምቹ ሁኔታ ወደ ልማት ለመቀየር እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንረባረብ  ይገባል ብለዋል ። በተለይ የልማትና የእድገት መሰረት የሆነውን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። በክልሉ የኢኮኖሚ መነቃቃት ሊረጋገጥባቸው ከሚገቡ አከባቢዎች አንዱ ጌዴኦ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የዞኑ ኢኮኖሚ የህዝቡን የመልማት ጥያቄ መመለስ እንዲችል ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ረገድ የክልሉ መንግስት ዞኑን በቅርበት እንደሚደግፍ ተናግረዋል። የአንድነትና የወንድማማችነት እንዲሁም የምስጋናና የመተሳሰብ በዓል በሆነው ዳራሮ ላይ በመገኝታቸው የተሰማቸውንም ደስታ ገልጸዋል። የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው ዳራሮ የጌዴኦ ብሔር ለበርካታ ከፍለ ዘመናት ሲያከብረው የኖረ የባህል እምነቱ መገለጫ የስነ ሕይወት ፍልስፍናና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። በህዝቡ መካከል ያሉትን ባህላዊ እሴቶች በማጎልበት የዞኑን ህዝቦች አንድነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ስራ ፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩንም ለማቃላል የዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል። በዚህም በቀጣይ አስርት አመታት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ወጣቶች እራሳቸውን እንዲችሉ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል። መንግስት በዞኑ ያለውን ድህነት ለማቃለል የሚያደርገውን ጥረት በመደጋፍ ረገድ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ የባሌ አስተዳደር መሪ አባጋዳ ዳንቦብ ማሩ በበኩላቸው ዳራሮን ከጌዴኦ ህዝብ ጋር ለማክበር ከተለያዩ አከባቢዎች የመጡ እንግዶችን አመስግነው ዳራሮ የሰላም ምልክት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሰላምን አጥብቆ እንዲይዝ አሳስበዋል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ እየታዬ ያለውን አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት የመቀበልና የእኔ ነው ብሎ የማሰብ መልካም ጅምር ተጠናክኖ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በበዓሉም ከ50 ሺህ የሚልቁ ሰዎች የታደሙ ሲሆን በፈረስ ጉግስና የተለያዩ ባህላዊ ይዘት ባላቸው ክዋኔዎች በድምቀት ተከብሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም