ፋብሪካው በሚሰጠን ነጻ አገልግሎት ኑሯችንን እየመራን ነው - የደብረ ብረሃን ነዋሪዎች

66
አዲስ አበባ   ጥር 17/2012  የደብረ ብርሐን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በነጻ በሚያቀርብላቸው የእንጨት ተረፈ ምርት አገልግሎት ኑሯቸውን መምራት እንዳስቻላቸው የዕድሉ ተጠቃሚዎች ተናገሩ። ፋብሪካው በበኩሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ባለው መልካም ግንኙነት ማህበረሰቡ ፋብሪካውን እንደባለቤት ያየዋል ብሏል። በስራ ቀናት ባንዱ ጥዋት የኢዜአ ሪፖርተሮች ወደ ምርት ከገባ ስድስት ዓመታትን ባስቆጠረው የደብረ ብርሐን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግቢ ድንገት ሲደርሱ ነበር በርካታ የከተማው ነዋሪ እናቶች በግቢው ውስጥ ሲርመሰመሱ ያገኟቸው። ወይዘሮ ጥሩወርቅ የሸዋማማ፣ ወይዘሮ ትኩነሽ ቅናቶና ወይዘሮ የሺ ሃይሉ በደብረ ብርሐን ደግሞ ከተማ የሚኖሩ የዕደሜ ባለፀጎችና በስፍራው ካገኘናቸው ነዋሪዎች መካከል ይገኙበታል። ሶስቱም አቅመ ደካሞች በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ፣ ነገር ግን በኑሯቸው አነስተኛ ገቢ ያላቸው፣ ቤተሰባቸውንም አረቂ በማውጣትና እንጀራ በመጋገር የሚደጉሙ መሆናቸውን ይናገራሉ። ፋብሪካው በከተማቸው መጥቶ ወደ ምርት መግባቱ የእንጨት ተረፈ ምርቱን በነጻ እንዲወስዱ ማድረጉም 'ኑሯችንን እንድንደጉምና ቤተሰብ እንድንመራ አድረጎናል፣ ከተጨማሪ ወጭ ታድጎናል፣ ሲቸግረንም ለገበያ በመሸጥ የዕለት ወጭ እንድንሸፍን አስችሎናል' ይላሉ። እኚህ የእድሉ ተጠቃሚዎች በሳምንት ስድስት ቀናት ወደ ፋብሪካው በመሄድ የቻሉትን ያህል የእንጨት ተረፈ ምርት በመሰብሰብ በጋሪ ጭነው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ነዋሪዎቹ ለራሳቸው አሰራር እንዲመችም በ14 ኮሚቴ የተደራጁ መሆኑንና ከየቀበሌው የተመለመሉትም በኢኮኖሚ አቅመ ደካማና ድጋፍ የሚሹ መሆናቸው ተረጋግጦ እንደሆነ የኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ መርሻ ይወጋ ይገልጻሉ። ፋብሪካው ለአቅመ ደካሞች 'የእናት ጓዳ ነው' ያሉት ወይዘሮ መርሻ፤ እርሳቸውም ሆነ ሌሎች የእድሉ ተጠቃሚ ነዋሪዎች የዕለት እንጀራ እንደሆናቸው ተናግረዋል። የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ደጀኔ ፋብሪካቸው ለአካበባው ማኅበረሰብ ከፈጠረው ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል በተጨማሪ ተረፈ ምርቱን በተለይም ለአቅመ ደካማ እናቶች በነጻ እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ለግበዓትነት ሚውለው ባህር ዛፍ በሚቆረጥባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የእንጨቱን ስር በነጻ ለአካባቢው ማህበረሰብ እንደሚሰጥ ገለጸዋል። በሚሰጠው የነጻ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትም ከማኅበረሰቡ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲፈጥር እንዳስቻለውና ሰው ፋብሪከውን እንደራሱ ባለቤት ቆጥሮ እየጠበቀላቸው ተናግረዋል ስራ አስኪያጁ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም