ህዝባዊ በዓላት የህዝብ ለህዝብ ግኙኝነት ያጠናክራሉ --- የዳራሮ በዓል ተሳታፊዎች

83
ዲላ (ኢዜአ) ጥር 17/2012  በተለያዩ ጊዜያት የሚከበሩ በዓላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙኝነትን በማጠናከር አንድነትን በመፍጠር ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን በዳራሮ በዓል ላይ የተገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ገለጹ ። አንዱ የሌላውን ባህልና እሴቶች መቀበሉ እንዲሁም በዓላትን በእኔነት መንፈስ በጋራ ማክበሩ ለዘላቂ ሰላም አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል:: አስተያየታቸውን ከሰጡት የበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ከምዕራብ ጉጂ ዞን የመጡት አቶ ኤሌማ ባርሶ ከጌዴኦ ብሔር ወንድሞቹ ጋር የዳራሮ በዓልን ማክበር በመቻላቸው  የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል ። በተለይ በጌዴኦና ጉጂ  መካከል የነበሩ አለመግባባቶችን ተፈትተው ዛሬ ዳራሮን በጋራ ማክበር መቻላቸው የህዝብ ለህዝብ ግኙኝነትን በማጠናከር አንድነታችን እንዲጎለብት የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል ። በጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ በሆነው የዳራሮ በዓል ላይ በመገኝቴ ከተለያዩ ሰዎችና ባህሎች ጋር እንዲተዋወቅ እድል ፈጥረልኛል የሚሉት ደግሞ ከወላይታ ዞን የመጡት አቶ ታደሰ ሜጋ ናቸው በወላይታ ጊፋታ ፣ በኦሮሞ ኢረቻ ፣ በጌዴኦ ዳራሮና በሌሎች መሰል በዓላት የሚሳተፉ ብሔር ብሔረሰቦች ግኙኝነታቸውን በማጠናከር አንድነታቸውን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል ። በተለይ ባህላዊ እሴቶቻችን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ያለውን ገንቢ ሚና እንደሚያጎለብት ተናግረዋል ። ከአዲስ አበባ የመጡት ወይዘሮ የትምወርቅ በየነ በበኩላቸው የዳራሮ በዓል ከዘመን መለወጫነቱ በተጓዳኝ ሰላምና አንድነት የሚሰበክበትና ህዝቦች ግንኝነታቸውን የሚያጠናክሩበት በዓል ሆኖ እንዳገኙት ገልፀዋል ። መሰል በዓላት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች መስፋፋታቸው አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ ከማድረጉም ባለፍ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል ። በዓሉ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በተገኙበት በዲላ ከተማ በድምቀት መከበሩ ይታወሳል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም