የጤና መድህን ኢንሹራንስ አባል በመሆናችን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት አስችሎናል ….የሀረና ወረዳ ተጠቃሚዎች

514

ጎባ ጥር 17/2012  (ኢዜአ ) የጤና መድህን ኢንሹራንስ አባል መሆናቸው ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው በባሌ ዞን የሀረና ወረዳ ተጠቃሚዎች ገለጹ።
አንዳንድ በመርሃ ግብሩ የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመድሃኒት አቅርቦትና በአገለልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያነሱትን ችግሮች ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ አስታውቋል  ፡፡

በሀረና ወረዳ የገርቢ ጋሎ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሂና አህመድ በሰጡት አስተያየት የጤና መድህን በአካባቢያቸው ከመጀመሩ በፊት የቤተሰባቸውን የህክምና ወጪ ለመሸፈን ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ 250 ብር የአባልነት መዋጮ በመክፈል ሁሉም የቤተሰብ አባላት የለምንም ችግር የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው  ብለዋል፡፡

ልጃቸውን ለማሳከም ለሆስፒታል አገልግሎትና ለመድኃኒት የከፈሉትን 8ሺህ ብር ወጪ የመድህን ኢሹራንስ አባል በመሆናቸው በጤና ጽህፈት ቤት አማካኝነት እንደተመለሰላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የፕሮግራሙ አባል አቶ አህመድ ናስር ናቸው፡፡

በደሎ መና ወረዳ የማኘቴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቃሲም አሚኖ በበኩላቸው በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፍሉት አነስተኛ የአባልነት መዋጮ እሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን በማሳከም ከከፍተኛ ወጪ መዳን ችለዋል ።

በጤና ተቋማት በኩል አልፎ አልፎ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ ተጠቃሚዎቹ ጠይቀዋል ።

የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሀምዛ ሱልጣን እንደገለፁት ከአራት ዓመታት በፊት በአራት ወረዳዎች ላይ ብቻ ሲተገበር የነበረ ፕሮግራም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተደረገው እንቅስቃሴ በ17 ወረዳዎች ላይ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል ።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ170 ሺህ  አባወራዎች በላይ መድረሱን ኃላፊው አስረድተዋል ።

በተለይ በተጠቃሚው ዘንድ ከአባልነት መታወቂያ፣ከአገልግሎት አሰጣጥና ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል ።

በኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ የሻሸመኔ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አመንሲሳ በበኩላቸው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤታቸው በምዕራብ አርሲ፤ባሌ፣ ቦረና፣ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተደረገው እንቅስቃሴ በተጠቀሱት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 69 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የመድህን አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት በመርሃ ግብሩ የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመድሃኒት አቅርቦትና በአገለልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያነሱትን ችግሮች በመፍታት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡