ዳሸን ባንክ መንግስት የቀየሰውን የስራ አጥ ቅነሳና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

122
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2012 ዳሸን ባንክ 'የኢትዮጵያ ታለንት ፓወር ሲሪየስ' የተሰኘውን ፕሮጀክት ጅማሮ በሃዋሳና አካባቢዋ ለሚገኙ ነዋሪዎች ይፋ ማድረጉን አስታውቋል ፡፡ የባንኩ የገበያና የደንበኞች ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስቻለው ታምሩ እንደገለጹት ባንኩ "መንግስት የቀየሰውን የስራ አጥ ቅነሳና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማገዝ አዲስ አበባን ጨምሮ ስድስት ክልሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ በተለየ ሁኔታ የስራ ፈጠራ ስልጠና፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አቅም ግንባታ፣ የከፍተኛ ትምህርት የፋይናንስ ድጋፍ፣ የቢዝነስ ክለብ ምስረታና የገበያ ትስስር ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችንም ይሰጣል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የንግድ  ሃሳቦች አማካሪው ዶክተር አቡሽ አያሌው በኢትዮጵያ 19 በመቶ የሚጠጋ ስራ ፈላጊ መኖሩን በመግለፅ መሰል ስልጠናዎች ሰዎች የራሳቸው ቀጣሪ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ በአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግና ስልጠናውን በተሳካ ሁኔታ የፈጸሙትንና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ  የፈጠራ ሃሳቦችን በማወዳደር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች ከግማሽ ሚሊዮን እስከ አንድ መቶ ሺ ብር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን የባንኩ መግለጫ ጠቅሷል። በሃዋሳ የተጀመረው የዳሸን ባንክ የኢትዮጵያ ታለንት ፓወር ሲሪየስ ፕሮጀክት በቀጣይ በአዳማ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም