የወጣቶች የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ላይ የሰለጠኑ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት እየተሰራ ነው

117

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2012 በወጣቶች የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ለመሳተፍ የሰለጠኑ ወጣቶችን በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የመስኖ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

ለፕሮጀክቱ ከ124 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለወጣቶቹ በሶስት አመት ውስጥ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የመስኖ ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሀሪ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ወጣቶቹ በመስኖ ልማት ስራ የሚሰማሩት በመጠናቀቅ ላይ ባሉና ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ባልሆኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች ነው።

እንደ አፋር፣ ሶማሌ፣ ምስራቅ አማራና ትግራይ ባሉ የከርሰ ምድር ውሃ ባለባቸውና አዳዲስ የመንግስት የመስኖ ፕሮጀክት ጭምር ወጣቶቹ እንዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ በሁሉም ክልሎች እንደሚተገበር ገልፀው፤ አሁን በመጀመሪያው ፓኬጅ በተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በአብዛኛው በስኳር ኮርፖሬሽን የተያዙ እንደ ኦሞ ኩራዝና ተንዳሆ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተንዳሆ ፈቃድ በተሰጠበት መሬት የምንጣሮ ስራ እየተሰራ መሆኑንና በኦሮሚያም ጊዳቦ ግድብ 1 ሺህ 400 ሄክታር መሬት እንደተሰጠ አሥረድተዋል።

እስካሁን ድረስ ከተለያዩ ክልሎች 5 ሺህ የሚደርሱ ወጣቶች በመስኖ ልማት ፕሮጀክት መሰልጠናቸውን ተናግረዋል።

የስራ ዕቅድ ዝግጅትና ወጣቶችን የማደራጀት ስራ መከናወኑንና የባንኮች ብድር ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ሚካኤል አብራርተዋል።

በመስኖ ልማት ስልጠና ያገኙ ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል የሚከናወኑ ስራዎች በመጪዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት  ኮሚሽነሩ፤ በዘርፉ ወጣቶችን የማሰልጠን ስራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የወጣቶች መስኖ ፕሮጀክት በእርሻና ተዛማጅ ሙያ ለተመረቁ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያግዝና የመስኖ ልማትን በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም