ወላይታ ድቻ ተጋጣሚውን አንድ ለባዶ አሸነፈ

84
ሶዶ፤ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) ዛሬ በተካሄደው የአስረኛው ሳምንት የወንዶች ፕሪሜየር ሊግ ጨዋታ ወላይታ ድቻ መቀሌ 70 እንደርታን አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸነፈ። ባለሜዳው ወላይታ ድቻ ከተከታታይ ሽንፈትና ነጥብ መጣል በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባ ጅፋርን  ሁለት ለአንድ  በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። ተጠባቂ በነበረው የዛሬ  የወላይታ ድቻ እና የመቀሌ 70 እንደርታ  ጨዋታ ለመሸናነፍ ያደርጉት ፉክክር የተመልካችን ቀልብ የሳበ ነበር። በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ እስከ 60ኛ ደቂቃ ድረስ ኳስ ላይ በተመሠረተ ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ ያደረገው መቀሌ 70 እንደርታ በተጋጣሚው ላይ የበላይነት ወስዶ ተከታታይ ሁለት የሚያስቆጩ የግብ ሙከራዎች አድርጓል። ወላይታ ድቻ ቀሪ ደቂቃዎችን ተጭኖ በመጫወት ፣በመከላከል፣ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ፥ በማጥቃትና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ብልጫ ወስዷል። በዚህ ሂደት በ79ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ መሬት ለመሬት በመምታት 25 ቁጥሩ ቸርነት ጉግሣ ነው ግቡን ያስቆጠረው። መቀሌ 70 እንደርታ ቢሸነፍም በ19 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። የወላይታ ድቻ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ በቡድኑ ውስጥ የተፈጠረው የማሸነፍ ስሜትና ፍላጎት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ። የመቀሌ አቻቸው ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው በቀጣይ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። በርካታ የስፖርት ደጋፊዎች በሜዳው ተገኝተው ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን አበረታተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም