የንግዱ ማህበረሰብ በሠላም ግንባታ ዙሪያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ ቀረበ

79

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የንግዱ ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

'የነጋዴው ማህበረሰብ ለአገራዊ የሰላም ግንባታ' በሚል መሪ ቃል ሚኒስቴሩ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በወቅቱ እንዳሉት፤ የንግዱ ማህበረሰብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከሚያከናውነው ተግባር በተጨማሪ ለሰላም ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል።

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የሰላም እጦት ተጎጂ እየሆነ ያለው የንግዱ ማህበረሰብ ሲሆን ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል የንግዱ ማህበረሰብ ለሰላም መስፈን ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አብራርተዋል።

''በተለይ ለግጭትና ለሁከት የሚዳርጉ ጉዳዮችን ከወዲሁ መለየት፣ መከላከልና ከተከሰቱም በኋላ መሸምገል ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የንግዱ ማህበረሰብ ሐብትና ንብረት እንዲጠበቅ ለማስቻል ከመንግስት ጎን በመቆም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠይቀዋል።

በተጨማሪ ማህበረሰቡ ከዘረኝነትና ከጎጠኝነት ራሱን በማራቅ የአገሩን ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበት አመላክተዋል።

በተለይ የአገርን ሰላም ለማናጋት የሚጥሩ ሰዎችን በመለየት በገንዘብም ሆነ በሌላ መንገድ ድጋፍ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሰዎች መካከል መልካም ግንኙነት ሲጠፋ የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና ሐብት የማፍራት መብትን የሚገድብ ስለሆነ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ወይዘሮ አልማዝ አስረድተዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን በሚያከናውነው ተግባራት ዙሪያ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ እንዳሉት፤ በሰላም እጦት ምክንያት በቅድሚያ የችግሩ ተጎጂና ተጋላጩ የንግዱ ማህበረሰብ ነው።

በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን በሚከናወኑ ተግባራት የንግዱ ማህበረሰብ በንቃት በመሳተፍ ትውልድን የመቅረጽ ስራ ላይ የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል አገሮች የነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ አገር አፍራሽ አጀንዳ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ አካላት መራቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በአገር ሰላም ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ካልቻለ የችግሩ ሰለባ ከሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት ቀጥሎ የንግዱ ማህበረሰብ መሆኑን  ሴት ነጋዴዎች ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም