የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሶስት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

112
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሶስት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ። በአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን የተመራ የሀገሪቷ የንግድ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቬዬሽን አካዳሚን ዛሬ ጎብኝቷል። በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጄኔራል ኤሌክትሮኒክስ (ጂኢ)፣ ሃኒዌል እና የአሜሪካ ንግድና ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስ ቲ ዲ ኤ) እህት ኩባንያ ከሆነው የሴብር ኮርፖሬት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነተ ተፈራርሟል። አየር መንገዱ ጂኢ ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ለሚያስመጣቸው ስድስት የቦይንግ 787-900 አውሮፕላኖች የሚያገለግሉ 13 የመለዋወጫ ሞተሮችን ከኩባንያው ይገዛል። አየር መንገዱ ለአውሮፕላን ሞተሮቹ ግዥ 444 ሚሊየን ዶላር፤ ለ10 ዓመታት ለሚቆይ የአውሮፕላኖች ጥገና አገልግሎት ደግሞ 473 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የኮንትራት ውል ከ ጂኤ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል። ሃኒዌል ከተሰኘው እና በመንገደኛ መገልገያ ምርቶች፣ በምህንድስና እና በኤሮስፔስ አገልግሎቶች ማቅረብ ሥራ ከተሰማራው ግዙፍ ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ደግሞ በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ማስፋፊያና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም መሰረት ለአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ማስፋፊያና ተያያዥ ሥራዎች የሚውል በአጠቃላይ የ17 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር መዋእለ ንዋይ የሚያወጡ ሁለት ስምምነቶች ተፈርመዋል። ሴብር ከተሰኘው ኩባንያ ጋር ደግሞ የ21 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር መዋእለ ንዋይ የሚፈስበት ውል ተፈርሟል። በዚህ ውል አማካኝነትም አየር መንገዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የደንበኛ ምዝገባና ማማከር  እና ፈጣን የበረራ ፕሮግራሞችና መሰል አገልግሎቶችን ከኩባንያው ይገዛል። በተመሳሳይ የሴብር እህት ኩባንያ ዩኤስ ቲ ዲ ኤ በበኩሉ ለአየር መንገዱ አንድ ሚሊየን ዶላር እርዳታ የሰጠ ሲሆን ገንዘቡም ለኢንፎርሜሽን ቴክኖክኖሎጂ ማስፋፊያ ተግባር እንደሚውል ተመልክቷል። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በዚህ ወቅት በሰጡት ቃል አየር መንገዱ የአውሮፕላን፣ የአውሮፕላን ሞተሮችና መገጣጠሚያ ቁሳቁሶችን የሚገዛው ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ለአውሮፕላን አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ወይም ኤሮስፔስ በራሱ አቅም ወደማምረት ተግባር መሸጋገሩን ተናግረዋል። ይህም አየር መንገዱ ለቦይንግ፣ ለቦምባርደር፣ ለሳፋር፣ ለጂኢና መሰል የአቪዬሽን ኩባንያዎች የተለያዩ የአውሮፕላን ዕቃዎችን አምርቶ ለመሸጥ የሚያስችል አቅም ይፈጥርለታል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ አየር መንገዱ ከተለያዩ የመስኩ አካላት ጋር የኢንቨስትመንት፣ የብድርና የቴክኒካል አጋርነት ፈጥሮ በትብብር ለመስራት አንደሚያስችለውም ተናግረዋል። አየር መንገዱ የሚሰጠውን አገልግሎት ከወረቀት በመውጣት ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክ ስርዓት ማሸጋገሩን ያወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ስመምነቶቹ በአይሲቲ ዘርፍ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና መተግበሪያዎችን ለመጠቀም እንደሚያስችሉም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጋር የተደረሱት ስምምነቶች አየር መንገዱ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማጎልበት እ.አ.አ በ2025 ሊደረስባቸው የተያዙትን ግቦች ለማሳካት ያግዘዋል ብለዋል። የአሜሪካ ምክትል የንግድ  ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያና አሜሪካ በንግዱ ዘርፍ ላላቸው ግንኙነት  ጉልህ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን እድገትና ትርፋማነት አድንቀዋል። የአሜሪካ ኩባንያዎች በአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም ልዑካኑ ከሚጎበኛቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል መካተቷ ኩባንያዎቹ ግንኙነታቸውን ከሀገሪቱ ጋር ለማጠናከር ፍላጎት ስላለቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸው የንግድ ሚዛን እንዲሻሻልም የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መስኮች መሳተፍ እንዳለባቸው ከሁለቱም ወገን ተነስቷል። የተለያዩ 23 የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ያቀፈው ልዑካኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አራት ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ ነው። ሀገራቱም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጋናና ኮትዲቯር ናቸው። የልዑካን ቡድኑ በሀገራቱ ያለውን መልካም የገበያ  እድሎችና ተግዳሮቶችን በማጤን የመጨረሻ ምልከታ ዘገባውን ለፕሬዝዳንት ትራንፕ ያቀርባል ተብሏል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም