የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ድርጅት ለአገር ሰላም መረጋገጥ ከወጣቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

88
አዲስ አበባ ጥር 16/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ድርጅት ለአገር ሰላም መረጋገጥ ከወጣቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ ። ወጣቶች በየአካባቢው የሚያጋጥመውን የሰላም መደፍረስ ለመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ድርጅት ዛሬ ከአዲስ አበባ የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት፣ ከወጣቶችና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላምና ብልጽግና ዙሪያ ውይይት አድርጓል። ከተመሰረተ ወራትን ያስቆጠረው ድርጅቱ ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ፣ በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉና የአገርን ሰላም በማስፈን ረገድም ሚናቸውን እንዲወጡ የማድረግ ዓላማ አለው። የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ወጣቶች የአገርን ሰላም ለማረጋገጥም ሆነ በኢኮኖሚው ራሳቸውን እንዲችሉ ይሰራል። ወጣቶች አገርን ለማሳደግና ሰላምን ለማረጋገጥ በትጋት እንዲሰሩ ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የአገርን ሰላም ለማስጠበቅና አገራዊ ለውጥ ለማምጣት ወጣቱን ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ወጣቱን መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል። አቶ ደረጀ ፋዬ የተባሉ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት ''ሰላም ከሁሉም የሚበልጥና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ ወጣቱን የሚያሳትፍ እንቅስቃሴ መጀመሩ መልካም ነው'' ብለዋል። ስራ አጥ ወጣቶች ተደራጅው ወደ ስራ መግባት ከቻሉና በኢኮኖሚው ራሳቸውን መደገፍ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ሰላሙም በዚያው ልክ ማረጋገጥ እንደሚቻልም ገልጸዋል። ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አበባው ካሳ ወጣቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግና አቅሙን ተጠቅሞ በመስራት ከራሱ አልፎ አገሩን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር እንደሚችል ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ድርጅት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግና የአገርን እድገት በወጣቱ ለማረጋገጥ የሚሰራ ድርጅት መሆኑ ተነግሯል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ስራ የጀመረው ድርጅቱ ወደፊት በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ ደቡብና በሶማሌ ክልሎች ከወጣቶች ጋር በመተባበር በሰላም ዙሪያ የመስራት ዕቅድ ይዟል። በመጪው አገራዊ ምርጫ አባላቱን በምርጫ ታዛቢነት እንደሚሳትፍ የገለጹት የድርጅቱ ፕሬዚዳንት፤ እድሜው ከ18 እስከ 38 የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አባል በመሆን ማገልገል እንደሚችል ተናግዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም